Thursday, April 16, 2015

የደርባን ደቡብ አፍሪካ ጥቃት ነገር

“የውጪ አገር ሰዎች ቅማሎች ናቸው። ወደመጡበት አገር መመለስ አለባቸው።” 
(የዙሉ ንጉሥ) ከዚህ ንግግር በኋላ ነው። ጥቃቶቹ የተጀመሩት። 

ታሪክ፦

በደቡብ አፍሪካዋ የደርባን ከተማ በስደተኛ አፍሪካውያን ላይ የተፈጸመው (እየተፈጸመ ያለው?) ጥቃት እጅግ አስደንጋጭ እና ዘግናኝ ነው። ብዙ አስተያየት ሰጪዎች፦
1. እንዴት አፍሪካውያን ሌሎች አፍሪካውያን ላይ እንዲህ ያለ የጅምላ ጥቃት ይፈጽማሉ?
2. ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካውያን ነጻነት ያንን ሁሉ ዋጋ ከፍላ እንዴት "ወርቅ ላበደረ ጠጠር" አደረጉ?
3. ነጮች ላይ እጃቸውን የማያነሱ ሰዎች ጥቁር ወገኖቻቸው ላይ ይህንን ግፍ እንዴት ይፈጽማሉ?
4. (እንደተለመደው) የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹ እንዲህ በአደባባይ በእሳት ሲጋዩ ለአፉ እንኳን ተቃውሞ አያሰማም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ፌስቡክ-ለፌስቡክ ሲንከባለሉ ነበር።

እንደኔ እንደኔ፦

ደቡብ አፍሪካውያኑ እንዲህ ላለ ጭፍጨፋ ከመብቃታቸው በፊት ጥንስሱ ብዙ ጊዜ የቆየ መሆን አለበት። ይህ እንደሚመጣም ምልክቶች ሳይታዩ የሚቀሩ አይመስለኝም። በደርባን ያሉ ስደተኛ አፍሪካውያን ነገሩን ለመከላከል ያደረጉት ነገር ካልነበረ እጅግ ይገርመኛል። በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ችግሩን ለመሸከም እግዜር ይርዳው እንጂ ኃላፊነቱን ከባድ ነው።
1. አፍሪካውያን በአፍሪካውያን ላይ፦ ጥላቻ ቀለም እና ድንበር የለውም። በተለይም ከአፓርታይድ የጨለማ ኑሮ ከወጡ የአንድ ሰው ዕድሜ እንኳን ያልሞላቸው ሰዎች ጎረቤታቸው ሱቅ የከፈተው የሌላ አገር ሰው የእነርሱን እንጀላ የሚበላ ጠላታቸው ቢመስላቸው አይገርምም። በአእምሮ የጎለመሰ ማኅበረሰብ ካልሆነ በርግጥም ለድህነት ያበቃው ጠላቱ ከሌላ አገር የመጣው ድሃ አፍሪካዊ ሊመስለው ይችላል። ከፖለቲካ አፓርታይድ ነጻ የወጣ፣ ከኢኮኖሚ አፓርታይድ ግን ነጻ ያልወጣ አገር ነው።
2. የኢትዮጵያን ውለታ በተመለከተ ተርታው ደቡብ አፍሪካዊ ያውቃል ብሎ ለመገመት እጅግ ይከብዳል። ሕዝብ በጅምላ የሚያስብበት አንድ ጭንቅላት የለውም። ደግሞም “ሕዝብ” ታሪክ ለመርሳት ብዙም ጊዜ አይፈጅበትም። ከዚህም ሁሉ በላይ ስለ ኢትዮጵያ ውለታ የሚያሳስባቸው ትልቅ አካል እንዳለ ሁሉ እንዴት ውለታችንን በሉ ብሎ መገረም ሚዛን አይደፋም።
3. “እንዴት ነጮች ገዚዎቻቸውን ሳይነኩ እኛን?” የሚለውም ብዙ ሚዛን የሚደፋ አይመስለኝም። ነጩን ነክቶ የት ሊገባ? እኛም ብንሆን ስንነካ የሚቆጣ፣ የሚናደድልን ቢኖር ማንም አይነካንም። ነጭ መሆን አለመሆን አልመሰለኝም ጉዳዩ። ደግሞም በኢኮኖሚ አፓርታይድ ውስጥ ያለ ሕዝብ አሁንም ገዢው ገንዘቡን የያዘው ነጩ መሆኑን አያጣውም። በአፍሪካ ካሉት አገራት በኢኮኖሚ አለመመጣጠን ግንባር ቀደም የሆነችው አንዷ ደቡብ አፍሪካ ናት። ጥቂት ነጭ ሀብታም፣ ብዙ ጥቁር ድሃ!!!
4. የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ? የተለመደ ነው። ምናልባትም ደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ ኢትዮጵያውያን ከሚበዙባቸው ዳያስጶራ ማኅበረሰቦች መካከል አንዱ እንደመሆኑ አደጋውን በዚህ ስሌት አያሰላውም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በሳውዲ አረቢያው ጊዜ የሆነውን ካየን፣ በየመን ላይ የወሰዱትን አቋም ካየን …. በደቡብ አፍሪካ እንዴት የተለየ ነገር ይጠበቃል? ተርታ የመንደር ቡድን ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን በሙሉ የሚወክል ኢትዮጵያዊ ድርጅት እስካልሆነ ድረስ እያደረገ ያለው ነገር ለተፈጥሮው የሚመጥነውን ብቻ ነው።

መፍትሔ?

የዳያስጶራው ሕይወት ጤናማ እና የተከበረ እንዲሆን ኢትዮጵያ መስተካከልና መከበር አለባት። ከዚህ በላይ ግን በናይጄሪያ እንደተጀመረው ዓይነት ደቡብ አፍሪካን የሚጎዳ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ማድረግ ለስደተኞቹ ጥሩ ዋስትና ይሆናል። አየር መንገዳቸው (SouthAfricanAirways) እንዳያርፍ ማድረግ ብቻ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተፎካካሪ የሆነና ብዙ ገበያ ያለው ነው። አፍሪካውያን ካመጹበት ሊያሽመደምዱት ይችላሉ። “ቦይኮት-ሳቅዝ-አፍሪካን-አዬርዌይስ/‪#‎BoycottSouthAfricanAirways‬” ማለት ነው። መቸም የኛዎቹ ጉዶች ያንን ያደርጋሌ ተብለው አይጠረጠሩም።

2 comments:

Anonymous said...

i fell so sory for this cruel inhumanities. please God help them

Anonymous said...

efrem betam new yetefakew

Blog Archive