Saturday, December 26, 2015

አይቴ ብሔሩ ለኦሮሞ፤ የኦሮሞ አገሩ እንግዲህስ የት ነው?

(ከኤፍሬም እሸቴ/ PDF) First Published on Thursday, October 30, 2014)
ገና ሃይ ስኩል ተማሪ ነኝ። የትምህርት ጥማቴ ገና ያልወጣልኝ። ተስፋዬን በደብተሬ ቅጠሎች መካከል አቅፌ የምዞር። ሰው ለመሆን የምማር። ተስፋዬን ከመናገሻ ተራራ ጀርባ የተሰቀሉ ይመስለኝ ነበር። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ፣ ከተራራው ገመገም ጀርባ የምትወጣው ፀሐይ ተስፋዬ በካዝና ከተቀመጠበት አገር የምትመጣ እንደሆነ ሁሉ ሙቀቷ ብርዴን፣ ጨረሯ ችግሬን ያስረሱኝ ነበር።
ገና ወፎች ጭውጭው ሲሉ የገነት ጦር ት/ቤት ሰልጣኝ ካዴቶች በዋናው አስፓልት ላይ የዕለቱን ስፖርት ለመከወን በሰልፍ ሲሮጡ፣ ከስከስ ጫማቸው ከአስፓልቱ ጋር ሲገናኝ የሚፈጥረው ድምጽ ሰፈራችንን ከእንቅልፍ ድብርቱ ያባንነዋል። ወደ ላይ እየሮጡ ሲሔዱ ሰምተናቸው ከ30 ደቂቃ በኋላ እየሮጡ ይመለሳሉ። ዋናውን ስፖርት ለመሥራት እየተሟሟቁ መሆን አለበት። ዋናውማ ካምፓቸው ውስጥ ነው። ከሰኞ እስከ አርብ ሁሌም ሲሮጡ ይሰማል። ወጣት የአገሬ ልጆች። ቆይተው “ተመረቁ” ይባልና ሰሜን ጦር ግንባር … ኤርትራ …. ትግራይ ….። ከዚያ መርዶ …።

Friday, December 18, 2015

በጥንቃቄ ልንመለከታቸው የሚገቡ “የጅምላ ጭፍጨፋ” ምልክቶች

(ኤፍሬም እሸቴ? READ IN PDF)
(ephremeshete@gmail.com/ www.adebabay.com)
እንደ ዳራ
እንዲህ ዓይነቱን ርዕሰ ጉዳይ አንስቶ በጥቂት ቃላት ለመተንተን መሞከር አንድም ጥልቅ ጥናትና ምርምር አንድም ብዙ ገጾች የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ቢሆንም ጥቂትም ቢሆን መናገር እና የተኛውን ማንቃት ምንም ካለመናገር ይሻላል በሚል ጥቂት ሐሳቦችን ለማካፈል ወደድኩ።
ይህ ጽሑፍ በሚጻፍበት ወቅት “አዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ የሚያስፋፋውን” ማስተር ፕላን በመቃወም በተለያዩ የኦሮሚያ አውራጃዎች ሕዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ እየወጣ፣ መንገድ እየዘጋ ብሶቱንና ምሬቱን እየገለጸ ነው። መንግሥት በበኩሉ የተለመደውን የኃይል ርምጃ በመውሰድ ብዙዎችን እየገደለ ነው። እስካሁንም ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች አስነብበዋል። የመንግሥት ባለሥልጣኖች በበኩላቸው መግለጫ በመግለጫ ላይ ቃለ ምልልስ በቃለ ምልልስ ላይ ይሰጣሉ። የሁሉም ሐሳብ ሲጠቃለል ደግሞ “ድርጊቱ የአሸባሪዎች ነው፤ ዋጋቸውን ነው የምንሰጣችሁ” ከሚል ማስፈራሪያ የዘለለ አይደለም።
ሌሎች ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ የኦሮሞው ሕዝብ ተቃውሞ የጠነከረበት የመንግሥቱ አስተዳደር ያለውን ችግር የብሔረሰቦች ግጭት ለማስመሰል በየቦታው ጥቃቶችን እያደረሰ መሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉ ሚዲያዎች እና የሰብዓዊ መብት ተንከባካቢዎች ያስረዳሉ። በተለይም በኦሮሞውና በአማራው መካከል ጦርነት ለመጫር ብዙ ቦታ እንደተሞከረና እንደከሸፈ ያስረዳሉ። ከዚህ በፊት የሁለቱ ብሔረሰቦች ግጭት በሚስተዋልባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ኦሮሞና አማራ ተማሪዎች አሁን ግን ከተጠመደላቸው ወጥመድ ለማምለጥ መቻላቸውን ይናገራሉ። አመያን በመሳሰሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግን አማራዎች መገደላቸው፣ ንብረታቸው በእሳት መጋየቱ በአንድ ወገን ሲዘገብ ይህንን ያደረገው ሰላማዊው ሕዝብ ሳይሆን በመንግሥት የተላኩ ካድሬዎች መሆናቸውን ሌሎች በተቃራኒው ያብራራሉ።