Friday, December 18, 2015

በጥንቃቄ ልንመለከታቸው የሚገቡ “የጅምላ ጭፍጨፋ” ምልክቶች

(ኤፍሬም እሸቴ? READ IN PDF)
(ephremeshete@gmail.com/ www.adebabay.com)
እንደ ዳራ
እንዲህ ዓይነቱን ርዕሰ ጉዳይ አንስቶ በጥቂት ቃላት ለመተንተን መሞከር አንድም ጥልቅ ጥናትና ምርምር አንድም ብዙ ገጾች የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ቢሆንም ጥቂትም ቢሆን መናገር እና የተኛውን ማንቃት ምንም ካለመናገር ይሻላል በሚል ጥቂት ሐሳቦችን ለማካፈል ወደድኩ።
ይህ ጽሑፍ በሚጻፍበት ወቅት “አዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ የሚያስፋፋውን” ማስተር ፕላን በመቃወም በተለያዩ የኦሮሚያ አውራጃዎች ሕዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ እየወጣ፣ መንገድ እየዘጋ ብሶቱንና ምሬቱን እየገለጸ ነው። መንግሥት በበኩሉ የተለመደውን የኃይል ርምጃ በመውሰድ ብዙዎችን እየገደለ ነው። እስካሁንም ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች አስነብበዋል። የመንግሥት ባለሥልጣኖች በበኩላቸው መግለጫ በመግለጫ ላይ ቃለ ምልልስ በቃለ ምልልስ ላይ ይሰጣሉ። የሁሉም ሐሳብ ሲጠቃለል ደግሞ “ድርጊቱ የአሸባሪዎች ነው፤ ዋጋቸውን ነው የምንሰጣችሁ” ከሚል ማስፈራሪያ የዘለለ አይደለም።
ሌሎች ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ የኦሮሞው ሕዝብ ተቃውሞ የጠነከረበት የመንግሥቱ አስተዳደር ያለውን ችግር የብሔረሰቦች ግጭት ለማስመሰል በየቦታው ጥቃቶችን እያደረሰ መሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉ ሚዲያዎች እና የሰብዓዊ መብት ተንከባካቢዎች ያስረዳሉ። በተለይም በኦሮሞውና በአማራው መካከል ጦርነት ለመጫር ብዙ ቦታ እንደተሞከረና እንደከሸፈ ያስረዳሉ። ከዚህ በፊት የሁለቱ ብሔረሰቦች ግጭት በሚስተዋልባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ኦሮሞና አማራ ተማሪዎች አሁን ግን ከተጠመደላቸው ወጥመድ ለማምለጥ መቻላቸውን ይናገራሉ። አመያን በመሳሰሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግን አማራዎች መገደላቸው፣ ንብረታቸው በእሳት መጋየቱ በአንድ ወገን ሲዘገብ ይህንን ያደረገው ሰላማዊው ሕዝብ ሳይሆን በመንግሥት የተላኩ ካድሬዎች መሆናቸውን ሌሎች በተቃራኒው ያብራራሉ።

ሐተታ
እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ፣ በአገራችን ይከሰታሉ ብዬ ከማልገምታቸው ነገሮች አንዱ “ኢትዮጵያውያን በቋንቋቸው ምክንያት” ወይም “ሰዎች በቋንቋ እና በወንዝ ተቧድነው ጦርነት ሊገጥሙ ይችላሉ” የሚለው ሐሳብ ነበር። በታሪኳ ጦርነት ተለይቷት የማያውቅ አገር ብትሆንም ቅሉ ማለት ነው። ይሁን እና የሕወሐት መንግሥት መንበረ ሥልጣኑን ከያዘ ወዲህ በሠራው ያላሰለሰ መንግሥታዊ ቅስቀሳ እና ሥር የሰደደ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች እርስበርሳቸው በጥርጣሬ የሚተያዩ ከመሆን አልፈው በብዙ ቦታዎች ጦር እስከመማዘዝ ደርሰዋል። አልፎ አልፎም “እናንተ የእኛ ወገን ሥላልሆናችሁ አገራችንን ለቃችሁ ውጡ” እየተባሉ ቤት ንብረታቸውን እየጣሉ እንዲሰደዱ ተደርገዋል። መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እና መዋቅሮች አንዱ የሌላኛው ሥጋት እና ጠላት ተደርጎ ከመሰበኩ የተነሣ የአንድ አገር ልጅነት ስሜት ቀዝቅዛ በጥርጣሬ እና በሥጋት መተያየት ልትሰለጥን ችላለች።
ጥያቄው መረር ያለም ቢሆን የግድ ልንጠይቀው ይገባል። በርግጥ ኢትዮጵያውያን በቋንቋቸው ምክንያት አደጋ ላይ ሊወድቁበት የሚችሉበት ዕድል አለ ወይ? ካለስ ምልክቱን በምን ማወቅ ይቻላል? “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዢ” እንደተባለው አይከሰትም በሚል ባዶ የዋህነት ነገሩን ከማጣጣል ከሌሎች አገሮች ታሪክ ተምረን ራሳችንን ልንጠብቅ የምንችልበትን ዘዴ መቀየስ ያስፈልገናል።
ግሪጎሪ ስታንተን (Gregory H. Stanton) የተባሉት የ “ጄኖሳይድ ዎች” (የዘር ማጥፋት ተመልካች) መሥሪያ ቤት ኃላፊና የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር “The 8 Stages of Genocide” በሚል ርዕስ ባጠናቀሩት እና በተለያዩ አገሮች የተከሰቱ የዘር ማጥፋት እና የጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀሎችን በማጥናት ቅድመ ጭፍጨፋ ያሉ ምልክቶቹን ባሰባሰበ ጥናታቸው ላይ ከጠቀሷቸው ስምንት ነጥቦች መካከል በተለይ ሦስቱ በአገራችን ያለውን ሁናቴ በአትኩሮት ለሚከታተል ለማንኛውም ሰው ማንቂያ ደወሎች ሆነው አግኝቻቸዋለኹ።

1.      ክፍፍል መፍጠር (Classification)
እንደ ግሪጎሪ ስታንተን ትንታኔ የጅምላ ጭፍጨፋ ከመፈጸሙ በፊት ከሌሎች አገሮች ለመረዳት እንደሚቻለው የጭፍጨፋዎች መጀመሪያው ክፍፍልን ከመፍጠር ይነሣል። “እኛ” እና “እነርሱ” የሚያስብል መስመር በሰዎች መካከል እንዲሰመር ማድረግ ማለት ነው። በሌላው ዓለም በዘር (ነጭ፣ ጥቁር፣ ቢጫ) ላይ የተመረኮዘው ክፍፍል ለዘመናት የኖረ ነው። ደቡብ አፍሪካውያን ነጭና ጥቁሮችን የለየው የዘር ግድግዳ ከፈረሰ 30 ዓመት እንኳን አልሞላውም። በአሜሪካ የነበረው በቀለም ላይ የተመሠረተ ክፍፍል (racial segregation) በአዋጅ ከታገደ 60 ዓመቱ ነው።
በኢትዮጵያ የብሔረሰብ (የቋንቋ) እንጂ የዘር (የቀለም) ልዩነት የለም። የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን የተለየ መሆንን አያሳይም። ነገር ግን በቋንቋ ላይ የተመሠረተውን ፌዴራሊዝም እንደ ምክንያት በመውሰድ የአገሪቱ ሕዝቦች በመታወቂያቸው ላይ ሳይቀር ብሔረሰባቸውና ቋንቋቸው ምን እንደሆነ እንዲገለጽ መደረጉ የልዩነት ምንጭና መነሻ እንደሆን እንዳስቻለ ብዙዎች ያምኑበታል።
አንድ ሰው የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ ክልል ነዋሪ መሆን ይችላል። ነገር ግን ከክልሉ ነዋሪነቱ አልፎ “ኦሮሞነቱ፣ አማራነቱ፣ ትግሬነቱ” በግልጽ እንዲጻፍ መደረጉ ማን የየትኛው ብሔረሰብ አባል መሆኑን በማያሻማ መልኩ እንዲገልጽና የሚዳኘው በዚያው ማንነቱ ብቻ እንዲሆን አስገድዶታል። ከሁለት ብሔረሰቦች የሚወለዱ ሰዎች ሳይቀሩ አንዱን እንዲመርጡ የሚደረጉበት ያልተጻፈ ሕግ ስለሰለጠነብን ማኅበረሰባችን ከመዋሐድ ወደ መነጣጠል እንዲያዘነብል ክፉ መሠረት ተጥሏል። ፕሮፌሰር ስታንተን እንዳሉት “Bipolar societies are the most likely to have genocide. በልዩነት የተወጠረ ማኅበረሰብ ለጅምላ ጭፍጨፋ የተጋለጠ ነው።”
በብዙ አጋጣሚዎች እንደሚታየው “ትግሬ ሁሉ ወያኔ አይደለም/ነው፤ ኦሮሞ ሁሉ ኦነግ አይደለም/ ነው፤ ኦሕዴድ ሲፋቅ ኦነግ ነው/አይደለም” የሚለው እሰጥ አገባ የሚያመለክተው ብዙ ነገር አለ። የአገራችን ፖለቲካ በአስተሳብና በመርሖ ላይ ሳይሆን በብሔረሰብ ቋንቋ እና ማንነት ላይ ብቻ የተመረኮዘ በመሆኑ አንድ ሰው በብሔረሰቡ ብቻ ወዳጅ ወይም ጠላት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። እንዲህ ያለው አሠራር በሕግ እስካልተወገደ ድረስ መጠፋፊያችንን በመታወቂያችን ተሸክመን እየዞር ነው ማለት ነው።

2.     ምልክቶችን መስጠት (Symbolization)
ናዚዎች አይሁዶችን ከሌላው ሕዝብ ለመለየት የዳዊት ኮከብ ያለበት ልብስ እንዲለብሱ አስገድደዋቸው ነበር። በዘመናችን እንኳን አይሲስ የተባለው ቡድን ክርስቲያኖችን ከማጥቃቱ በፊት በየቤታቸው ላይ በቀይ ቀለም ምልክት ማድረጉን እንመለከታለን። የካምቦዲያው ኬመን ሩዥ መንግሥት በምሥራቁ የአገሪቱ ግዛት የሚገኙ ዜጎቹን ከመጨፍጨፉ አስቀድሞ መለያ እንዲሆናቸው ሰማያዊ የአንገት ልብስ እንዲለብሱ አድርጓቸው ነበር። በአገራችን እዚህ ደረጃ የሚደርስ ፍረጃ የለም። ነገር ግን ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ እና በስማቸው ብቻ “ተጠርጣሪዎች” እና “ተቃዋሚዎች” ተደርገው የሚወሰዱበት ደረጃ መድረሱን ተዳግሚ ሲገለጽ እየሰማን ነው። ኮከቡና ቀይ ምልክቱ እንዲሁም የአንገት ልብሱ ባይኖርም ስምና ቋንቋ የጠላትነት ምልክት ተደርገው መወሰዳቸውን ለመገንዘብ ብዙም አያዳግትም። አቶ ስዬ አብርሃ “የእስር ቤቶቻችን ቋንቋ ኦሮምኛ ሆኗል” በማለት ወሕኒ ቤቶች በኦሮሞ ተወላጆች መሞላታቸውን መጥቀሳቸውን ልብ ይሏል።

3.     ከስብዕና ውጪ ማድረግ (Dehumanization)
የጅምላ ጭፍጨፋዎች ከመካሄዳቸው በፊት ተጨፍጫፊውን ወገን ከሰውነት ተራ የሚያወጡና ከስብዕና የሚያወርዱ ተግባራት (Dehumanization) እንደሚፈጸሙ ግሪጎሪ ስታንተን በሦስተኛ ነጥባቸው ያብራራሉ። ለምሳሌ ናዚ ጀርመኖች አይሁዶችን “አይጦች” እና “ተባዮች” ("rats" or "vermin") ሲሏቸው፤ የሩዋንዳ ሑቱዎች ደግሞ ቱትሲዎችን “በረሮዎች” (cockroaches) ይሏቸው ነበር። ሁለቱ ታሪኮች የሚያመሳስላቸው አንድ ሁነኛ ነጥብ ሊያጠፉ የፈለጉትን ቡድን “በሽታ፣ ተባይ፣ ነቀርሳ” አድርጎ የመጥራቱ ሁኔታ ነው።
ይህንን የፕሮፌሰር ስታንተንን ሐሳብ አንብቤ በምቆዝምበት ወቅት የመንግሥት የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣውን ሕዝብ “ጋኔል፣ አጋንንት፣ ሰይጣን፣ ጠንቋይ” እያለ የሰጠውን መግለጫ ተመለከትኩ። ሌሎቹ የመንግሥት ኃላፊዎች “የጥፋት ኃይሎች፣ አሸባሪዎች፣ ወንጀለኞች፣ ዘራፊዎች” ያሉትን ነው ጌታቸው ሃይማኖታዊ በሆነ ምልከታ ያመሳሰለው።
አገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የተደረጉ ፍጅቶችን ስንመለከት አንዱ ሌላውን የሚጠራበት መንገድ፣ አንዱ ለሌላው ምንም ሐዘኔታ እንዳይኖረው ሊያደርግ እንደሚችል ለመረዳት ያስችላል። ሕወሐትና ሻዕቢያ ጦርነት የገጠሙትን የኢትዮጵያ (“የደርግ ኢሰፓ”) ወታደር “አድጊ” ወይም “አህያ” እያሉ እንደሚጠሩት የአደባባይ ምስጢር ነው። ሥልጣን ከያዙ በኋላም የሚቃወማቸውን ሁሉ ለዜጋቸው በማይመጥን አጸያፊ ቅጥያዎች ሲያንቋሽሹ መስማት የተለመደ ተግባር ነው። መንግሥታዊ ቴሌቪዢኖችና ራዲዮኖች ዕድሜ ሳይለዩ የሚያስተላልፉት እንዲህ ያለውን መልእክት ነው።
በዚህ ፕሮፓጋንዳ ገና ከልጅነቱ ልቡና መንፈሱ የታጠበ (ብሬይን ወሽድ የሆነ) ማንም መሳሪያ አንጋች ሌላውን ወገን ለመፍጀት ብዙም ማመዛዘን አያስፈልገውም። ምክንያቱም የሚያቆስለው፣ የሚገድለው ሰው ወገኑ፣ ወንድሙ/ እህቱ፣ የአገሩ የኢትዮጵያ ልጅ ሳይሆን “ጋኔል፣ ሰይጣን፣ አድጊ፣ ነፍጠኛ” እንደሆነ አስቀድሞ ተነግሮታልና። እንዲህ ያለውን ፍጅትና ጭፍጨፋ ባለስልጣኖቹ “ልክ ማስገባት” በሚል ቃል አጠይመው ይገልጹታል።

ተጨማሪ ነጥቦች
ፕሮፌሰር ስታንተን ከ4ኛ እስከ 8ኛ ድረስ ካነሷቸው ተጨማሪ ነጥቦች በ4ኛ ላይ የጠቀሰው መደራጀት (Organization) የሚለው ነው። የጅምላ ጭፍጨፋ የሚያደርጉ አካላት በሙሉ የተደራጁ፣ ያቀዱ እና መሪ ያላቸው ቡድኖች ናቸው። ከናዚ ጀመርን እስከ ሩዋንዳ ኢንተርሐሙዌ፣ ከአይሲስ እስከ ካምቦዲያው ኬመንሩዥ ያለውን ለአብነት መጥቀስ ይገባል።
ከዚህም ባሻገር የተደራጁ ቡድኖች ተከታዮቻቸውን ለተግባር ዝግጁ የሚያደርጉት ነገሮችን በመወጠርና በማካረር (5ኛው ነጥብ Polarization) ሲሆን  በእነርሱ መመዘኛ ጠላት ናቸው የሚሏቸውን አካላት ማንነት በመለየት ለጥፋታቸው መዘጋጀት (6ኛው ነጥብ Preparation) እንዲሁም የማይቀረውን ጭፍጨፋ (7ኛው ነጥብ Extermination) ማካሔድ የጅምላ ጭፍጨፋ ተጨማሪ ነጥቦች ናቸው።
መለስ ዜናዊ በጋምቤላ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸውን የጅምላ ፍጅት አስመልክቶ ሲናገር ድርጊቱን ሽምጥጥ አድርጎ እንደካደው ሁሉ በሌሎች አገሮችም የተካሄዱ ፍጅቶችን በተመለከተ ፈጻሚዎቹ አለመቀበላቸውና መካዳቸው (8ኛው ነጥብ Denial) እንደሚያመሳስላቸው ፕሮፌሰር ስታንተን ያስረዳሉ።
ይሁን እንጂ “ተሸፋፍነው የሠሩትን ገልጦ የሚያይ አምላከ አለ” እንዲል ተረታችን የንጹሐን ደም እንደ አቤል ደም መጮኹና ደም አፍሳሹን ማጋለጡ አይቀርም። ትናንትም ነገም። ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ብሎ የማይሆን ወንጀል ከመሥራት መቆጠብ አዋቂነት ነው። በኦሮሚያ፣ በጎንደርና በመተማ፣ በጋምቤላና በኦጋዴን ወዘተ የፈሰሰውና በመፍሰስ ላይ ያለው የኢትዮጵያውያን ደም መቆም አለበት። የጦር ኃይል ብቻውን ወንበር እንደማያረጋ ከራሳችን ታሪክ መማር አለብን።

በመጨረሻ
በዘመነ መርዶክዮስ ሐማ በሚባል ሰው አማካኝነት አይሁድን በሙሉ የማጥፋት አዋጅ ታወጀ። ይሁን እንጂ በቤተ መንግሥቱ፣ ከንጉሡ ቀኝ የምትቀመጠው አስቴር ይሑዲት ነበረች። ቀጥሎ ያለው ለእርሷ የተላከ መልእክት ነው።
" .... ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት ... አንቺ፦ በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?" (መጽሐፈ አስቴር  4:13-14)። በእውነቱ በዚህ ዘመን ላለ ሰው ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው። ጆሮ ያለው ይስማ!!! በተለያየ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናት ቆም ብለው ለመመልከት አሁንም አልመሸም። መጠን ከሌለው በራስ መመካትና መታበይ ይልቅ አስተዋይነት ትልቅ ዋጋ እንዳለው ለመገንዘብ የኅሊናን ጓዳ መፈተሽ ይሻላል። ሌላ መካሪ ሳይመጣ እግዚአብሔር ኅሊና  የሚባል ዳኛ ፈጥሮ ሰጥቶናል። የኅሊናችንን ዳኝነትና መልእክት እናዳምጥ።

ይቆየን፤ ያቆየን

5 comments:

Unknown said...

Arif tentena

Abebe Furi said...

ወንደሜ ዲ/ን ኤፍሬም
በእውነት ባነሳሃቸው ነጥቦች እና በትንታኔህ እስማማለሁ ስጋቶችህንም እኔን ጨምሮ ብዙዎች የሚጋሩት ለመሆኑ አንዳች ጥርጥር የለኝም። ሰው ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ ሲሰማውና ሲግባባበት በኖረው ቋንቋ ያለምንም ቱርጁማን ሲዳኝ፤ሲማር፤ሲሰብክና ሲሰበክለት፤ ቋንቋውን ማሕበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራቱን ማከናወኛ አደርጎ ሲጠቅምበት ማየት የዚያን ቋንቋ ተጠቃሚ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ወደዚያ ህዝብ መልዕክት እንዲደርስለት የሚፈልግን አካል ሁሉ ደስ ሊለው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ መንገድ ነውና። በእርግጥ አንዱ ቋንቋ ከሌላው በተደራሽነቱ ሊበልጥ ይችል ይሆናል ሁሉም ቋንቋዎች ግን የዚያን ማህበረሰብ ባህልና ታሪክ ለማስረዳት በቂ ናቸው ብዬም አምናለሁ። ኢትዮጵያችን ውስጥ ግን ይህ ለረጅም ጊዜ ስላልነበረና በቅርቡ (እውነተኛ ምክንያቱ ሌላ ቢሆንም) “የተሰጠ” “ነፃነት” በመሆኑ ከአስፈላጊነቱ ጀምሮ እስከአጠቃቀሙ ድረስ ጎራ ለይተን በሃሳብ እንቦቀስበት ከያዝን እነሆ ድፍን ኢሕአዴግ ሞላን። በተለይ በሁሉም ጎራ(ገዢውምና ተቃዋሚው፤ ብሄርተኛውና ህብረብሄራዊው) ያሉት የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ በኩል ያበረከቱት ውድመት በሌላው በሁሉም ዘርፍ ከሰጡን ጥፋት በእጅጉ ይበልጣል። አለመታደል ሁኖ ምዕመናኖቻቸው(እኔም አለሁበት) የዘመናችንን የሐይማኖት አባቶች ከፖለቲካ ጥገኝነት ነፃ ናቸው ብሎ ስለማያምን በፖለቲካ ልሂቃኑ ሊሞሉ ያልቻሉ ክፍተቶችን እንሙላ እንኮን ቢሉ ሰሚ ጆሮ አያገኙም። የሀገሪቱ ምሁራን ግን ከዚህ የተለየ ነገር ማድረግ የሚችሉ ይመስለኛል። አደጋውን ከተለያዩ ሀገራት ልምድ አንፃር ለህዝብ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር ማስገንዘብ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። በዚህ ረገር የኦሮሞ የጥናት ማህበር (Oromo Studies Association) እያደረገ ያለው ተግባር ልምድ ሊቀሰምበት የሚገባ ሳይሆን አይቀርም። እዚህ መድረክ ላይ የሚቀርቡና በደንብ የተብላሉ ሃሳቦች ናቸው በብዛት ፖሊሲውች፤ የመታገያ ሃሳቦች፤ የኪነ-ጥበብ ስራዎች(ዘፈን፤ግጥም፤ድራማ ወዘተ) ጭብጦች ሆነው የምናያቸው። (የነ ያጫሉንና የጃምቦ ጆቴን ዘፈን ልብ እንበል)
ሌላውና ዋነኛው ህዝብን በሁሉም ረገድ ኑሮውን እይኖሩ ሕመሙን እየታመሙ ቁስሉን እየቆሰሉ ሞቱንም ሳይቀር እይሞቱ ሊአያስተምሩት የሚግባቸውና እንደየሥራቸው ህዝብ የሚያከብራቸውና የሚሰማቸው የኪን-ጥበብ ባለሙያዎች ነበሩ። ዛሬ ዛሬ ባለሙያው ህዝብን ከማማረር ማሳቅ የሻላል ብሎ ይሁን ኑሮውን ሳይሆን ህልሙን ላሳየው ብሎ ብቻ የጥበብ አድባር በሳቅ እይተንከተከትች በ“ፍቅር” እየተብከነከነች አለች። የኪን-ጥበብ ባለሙያዎችን ሥራ ለማሳነስ ፈልጌ አይደለም ጌዜው የሚጠይቀውና እየመጣ ያለው አደጋ አሁን እያበረከቱት ካለው አስትዋፅኦ በእጅጉ ከፍ ያለ ሥራ እንደሚጠይቅ ለማስገንዘብ እንጂ። የኪን-ጥበብ ባለሙያዎች ከህዝብ ቀድመው በሀገርና በህዝብ ላይ ሊመጣ ያለውን አደጋ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው ካልተነበዩ ተራው ህዝብ በፍጥነት ፍጹም ስህተት ለሆነ መርጃ ሰለባ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የኪን-ጥበብ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው በሚያነሷቸው ርዕሶች ዙሪያ ህዝብ ቢወያይ በተነሳው ጉዳይ ላይ መግባባት እንካን ባይቻል አንዱ የሌላኛውን ወገን ሃሳብ ለማድመጥ ዕድል ይፈጠርለታል። ብዬ እኔ አምናልሁ

Abebe Furi said...

ወንደሜ ዲ/ን ኤፍሬም
በእውነት ባነሳሃቸው ነጥቦች እና በትንታኔህ እስማማለሁ ስጋቶችህንም እኔን ጨምሮ ብዙዎች የሚጋሩት ለመሆኑ አንዳች ጥርጥር የለኝም። ሰው ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ ሲሰማውና ሲግባባበት በኖረው ቋንቋ ያለምንም ቱርጁማን ሲዳኝ፤ሲማር፤ሲሰብክና ሲሰበክለት፤ ቋንቋውን ማሕበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራቱን ማከናወኛ አደርጎ ሲጠቅምበት ማየት የዚያን ቋንቋ ተጠቃሚ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ወደዚያ ህዝብ መልዕክት እንዲደርስለት የሚፈልግን አካል ሁሉ ደስ ሊለው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ መንገድ ነውና። በእርግጥ አንዱ ቋንቋ ከሌላው በተደራሽነቱ ሊበልጥ ይችል ይሆናል ሁሉም ቋንቋዎች ግን የዚያን ማህበረሰብ ባህልና ታሪክ ለማስረዳት በቂ ናቸው ብዬም አምናለሁ። ኢትዮጵያችን ውስጥ ግን ይህ ለረጅም ጊዜ ስላልነበረና በቅርቡ (እውነተኛ ምክንያቱ ሌላ ቢሆንም) “የተሰጠ” “ነፃነት” በመሆኑ ከአስፈላጊነቱ ጀምሮ እስከአጠቃቀሙ ድረስ ጎራ ለይተን በሃሳብ እንቦቀስበት ከያዝን እነሆ ድፍን ኢሕአዴግ ሞላን። በተለይ በሁሉም ጎራ(ገዢውምና ተቃዋሚው፤ ብሄርተኛውና ህብረብሄራዊው) ያሉት የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ በኩል ያበረከቱት ውድመት በሌላው በሁሉም ዘርፍ ከሰጡን ጥፋት በእጅጉ ይበልጣል። አለመታደል ሁኖ ምዕመናኖቻቸው(እኔም አለሁበት) የዘመናችንን የሐይማኖት አባቶች ከፖለቲካ ጥገኝነት ነፃ ናቸው ብሎ ስለማያምን በፖለቲካ ልሂቃኑ ሊሞሉ ያልቻሉ ክፍተቶችን እንሙላ እንኮን ቢሉ ሰሚ ጆሮ አያገኙም። የሀገሪቱ ምሁራን ግን ከዚህ የተለየ ነገር ማድረግ የሚችሉ ይመስለኛል። አደጋውን ከተለያዩ ሀገራት ልምድ አንፃር ለህዝብ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር ማስገንዘብ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። በዚህ ረገር የኦሮሞ የጥናት ማህበር (Oromo Studies Association) እያደረገ ያለው ተግባር ልምድ ሊቀሰምበት የሚገባ ሳይሆን አይቀርም። እዚህ መድረክ ላይ የሚቀርቡና በደንብ የተብላሉ ሃሳቦች ናቸው በብዛት ፖሊሲውች፤ የመታገያ ሃሳቦች፤ የኪነ-ጥበብ ስራዎች(ዘፈን፤ግጥም፤ድራማ ወዘተ) ጭብጦች ሆነው የምናያቸው። (የነ ያጫሉንና የጃምቦ ጆቴን ዘፈን ልብ እንበል)
ሌላውና ዋነኛው ህዝብን በሁሉም ረገድ ኑሮውን እይኖሩ ሕመሙን እየታመሙ ቁስሉን እየቆሰሉ ሞቱንም ሳይቀር እይሞቱ ሊአያስተምሩት የሚግባቸውና እንደየሥራቸው ህዝብ የሚያከብራቸውና የሚሰማቸው የኪን-ጥበብ ባለሙያዎች ነበሩ። ዛሬ ዛሬ ባለሙያው ህዝብን ከማማረር ማሳቅ የሻላል ብሎ ይሁን ኑሮውን ሳይሆን ህልሙን ላሳየው ብሎ ብቻ የጥበብ አድባር በሳቅ እይተንከተከትች በ“ፍቅር” እየተብከነከነች አለች። የኪን-ጥበብ ባለሙያዎችን ሥራ ለማሳነስ ፈልጌ አይደለም ጌዜው የሚጠይቀውና እየመጣ ያለው አደጋ አሁን እያበረከቱት ካለው አስትዋፅኦ በእጅጉ ከፍ ያለ ሥራ እንደሚጠይቅ ለማስገንዘብ እንጂ። የኪን-ጥበብ ባለሙያዎች ከህዝብ ቀድመው በሀገርና በህዝብ ላይ ሊመጣ ያለውን አደጋ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው ካልተነበዩ ተራው ህዝብ በፍጥነት ፍጹም ስህተት ለሆነ መርጃ ሰለባ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የኪን-ጥበብ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው በሚያነሷቸው ርዕሶች ዙሪያ ህዝብ ቢወያይ በተነሳው ጉዳይ ላይ መግባባት እንካን ባይቻል አንዱ የሌላኛውን ወገን ሃሳብ ለማድመጥ ዕድል ይፈጠርለታል።

Anonymous said...

እኔምለው… ከ75 ሰው በላይ ተገድሎ… አንተም ራስህ ከ50 በላይ ብለህ… ከሁሉ አስቀድመህ ማዘንህን መግለፅ አትችልም ነበር፡፡ ወይስ በሀይማኖታችሁ ያስቀጣል

Adebabay A said...

Dear anonymous,
Today, 12/21/2015; 8:03pm Eastern USA time, ESAT said the dead are 85.