Friday, April 22, 2016

ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም (ዘየሐጽብ በወይን ልብሶ)

የራስ-ከራስ-ጋር-ጨዋታ

እየደጋገምኩ ባነበብኩት እና ዜማውን ባስታወስኩ ቁጥር አንዳች ስሜት ልቤን ያናውጸዋል።
የሆሳዕና ሥርዓተ ማኅሌት ተፈጽሞ ሥርዓተ ቅዳሴው ከመጀመሩ በፊት ሥርዓተ ዑደት በሚፈጸምበት ወቅት አራቱም ወንጌላት ይነበባሉ። ይኸውም ሊቃውንቱ የዕለቱን ድጓ እየቃኙ ይመራሉ፣ ዲያቆናቱም ከመዝሙረ ዳዊት የዕለቱን በዓል የተመለከተ ምስባክ ይሰብካሉ፣ ካህናቱም በዓሉን የተመለከተ ወንጌል በዐራቱም መዓዘን እያነበቡ ቤተ መቅደሱን አንድ ጊዜ ይዞሩታል፡፡
የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ከመነበቡ በፊት የሚዜመው ዜማ የክርስቶስን መከራ ሞቱን የሚያጠይቁ ኃይለ ቃሎች ይዟል። ሊቃውንት አባቶቻችን በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 49 ላይ የሚገኘውን ጻድቁ ያዕቆብ ልጆቹን የነገራቸውን ታሪክ በማንሣት፣ ለይሁዳ የተነገረውን እና ስለ ክርስቶስ የተተነበየውን በማመስጠር ያስቀመጡበት ድንቅ ምሥጢር ነው።

Monday, April 18, 2016

ሰማዕታቱ እነሆ አንድ ዓመታቸው

በሊቢያ ሰማዕትነት የተቀበሉት ወንድሞቻችን ይህንን የድል አክሊል ከተቀዳጁ እነሆ አንድ ዓመት ሆናቸው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ስለ ሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን በዓለም ፊት የተቀበሉ የተዋሕዶ ፍሬዎች ናቸውና ገድላቸውን ቤተ ክርስቲያን በታላቅ አንክሮ ትመለከተዋለች። ከሁሉ ከሁሉ ሰማዕትነቱን የተቀበሉበት መንገድ እና ዜናው ለዓለም የተዳረሰበት ሁኔታ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የነፍስ ልብ ሰቅስቆ የወጋ፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ መላውን ዜጋ ያነቃነቀ ጉዳይ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እነሆ የኢትዮጵያውያን ስደት፣ እንግልት፣ እስራትና ሞት በአስደንጋጭ መልኩ የዕለት ተዕለት ዜናችን ሆኗል። ከኃዘኑ ብዛት የተነሣ ነፍሳችን የመከራ ዜናን ለመደችው። "ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን" (ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥36) እንደተባለው ነው። ባለፈው ዓመት የሰማዕታቱን ነገር አስመልክቶ በአደባባይ ካሰፈርኩት ላካፍል።

Thursday, April 14, 2016

ኦርቶዶክሱ ራሱን ሁለተኛ ዜጋ ያደረገበት አካሔድ

(ኤፍሬም እሸቴ) 
 እንደ ዳራ
ሁለት የባፕቲስት ሚሲዮን እምነት ተከታዮች የሆኑ ፓስተሮች ባለፈው የጥምቀት ሰሞን አገራችንን መጎብኘታቸውን እንዲሁም ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋርም መነጋገራቸውን በፎቶግራፎች አስደገፈው ያወጡት ዜና ያትታል። ዜናውን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ከፍተኛ መነጋገሪያ እንዲሆን ያደረገው የሁለቱ ፓስተሮች ጉብኝት ሳይሆን እንገነባዋለን ያሉት የ50ሺህ አብያተ ጸሎት ጉዳይ እንዲሁም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ናቸው በተባሉት በአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ላይ (ያውም በፓርላማው መንበራቸው ላይ እንደተሰየሙ) ከዳርና ከዳር ጠምደው ጸሎት ሲያደርጉላቸው የሚያሳየው ፎቶግራፍ ነው። http://www.bpnews.net/46636/layman-plans-for-50000-churches-in-ethiopia
ከዚህም ባሻገር የጉዞ ዘገባቸው ያነሣቸው አስገራሚ ነጥቦች አሉ።
1ኛ. የጉዞ ወጪያቸውን የሸፈነላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑ፣
2ኛ. ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሁም ከአየር መንገድ ኃላፊዎችና በአሜሪካ ከኢትዮጵያ አምባሳደር ጋር መነጋገራቸው እና እነርሱም በሁሉም ነገር እንደሚተባበሯቸው ቃል መግባታቸው መገለጹ፣