Monday, April 18, 2016

ሰማዕታቱ እነሆ አንድ ዓመታቸው

በሊቢያ ሰማዕትነት የተቀበሉት ወንድሞቻችን ይህንን የድል አክሊል ከተቀዳጁ እነሆ አንድ ዓመት ሆናቸው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ስለ ሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን በዓለም ፊት የተቀበሉ የተዋሕዶ ፍሬዎች ናቸውና ገድላቸውን ቤተ ክርስቲያን በታላቅ አንክሮ ትመለከተዋለች። ከሁሉ ከሁሉ ሰማዕትነቱን የተቀበሉበት መንገድ እና ዜናው ለዓለም የተዳረሰበት ሁኔታ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የነፍስ ልብ ሰቅስቆ የወጋ፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ መላውን ዜጋ ያነቃነቀ ጉዳይ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እነሆ የኢትዮጵያውያን ስደት፣ እንግልት፣ እስራትና ሞት በአስደንጋጭ መልኩ የዕለት ተዕለት ዜናችን ሆኗል። ከኃዘኑ ብዛት የተነሣ ነፍሳችን የመከራ ዜናን ለመደችው። "ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን" (ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥36) እንደተባለው ነው። ባለፈው ዓመት የሰማዕታቱን ነገር አስመልክቶ በአደባባይ ካሰፈርኩት ላካፍል።
ሰማዕትነት የቤተ ክርስቲያን ጌጥፀ ሰማዕታትም የቤተ ክርስቲያን ምርጥ ዘሮች ናቸው። በረከታቸው፣ አማላጅነታቸው አይለየን።
++++
“የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን [ምርጥ] ዘር ነው” (ጠርጠሉስ)
(ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ)
ጠርጠሉስ የተባለውና በ2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (160 AD - 220 AD) የነበረው ታላቅ ፀሐፊና የክርስትና ጠበቃ ስለ ሰማዕታት ደም በተናገረበት ሥፍራ ያስቀመጠው ነው። ተርቱሊያን/ Tertullian ወይም በእኛ አጠራር ጠርጠሉስ የሚባለው ሊቅ ከመጀመሪያዎቹ የክርስትና አባቶች ጋር የሚቆጠር እንዲያውም የላቲኖች (በላቲን የምትናገረው፣ የምትጽፈው) ቤተ ክርስቲያን ወይም የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አባት ተብሎ መጠራት እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ሊቅ ነበር። በእኛ በኦርቶዶክሳውያንም ሆነ በካቶሊኮቹ ዘንድ ብዙም ስሙ ሲጠቀስ የማይሰማው ከጻፋቸው ጽሑፎች መካከል ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የወጡ ስላሉበት ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ሊቅ በዚህ ሥፍራ መጥቀስ የፈለግኹት አገሩና ምንጩ የሰሜን አፍሪካ (የዛሬዋ ቱኒዚያ) አካል በሆነችው በካርቴጅ የተገኘ በመሆኑ ጭምር ነው።
እናም ይህ አፍሪካዊ ሊቅ እንዲህ አለ፦ “ …. የበለጠ በገደላችሁን መጠን የበለጠ እንኖራለን (አለን)። የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን [ምርጥ] ዘር ነው። … ጭካኔያችሁ የሚያሳየው እኛን ከምትከሱበት ወንጀል ነጻ መሆናችንን ነው። … እናም ዓላማችሁን ከንቱ ታደርጋላችሁ። ምክንያቱም ስንገደል (ስንሞት) የሚመለከቱ ሰዎች ለምን እንደምንገደል ይገረማሉ። እንደ ወንጀለኛ እና እንደ ተናቀ ሰው ሳይሆን እናንተ እንደምታከብሯቸው ሰዎች በክብር እንሞታለንና። [ስንገደል/ ስንሞት የሚመለከቱ ሰዎች] እውነቱን ሲረዱ ደግሞ እኛን ይመስሉናል/ ከእኛ ጋር አንድ ይሆናሉ (ይቀላቀሉናል)።”

1 comment:

Anonymous said...

በረከታቸው ይደርብን!የእነሱን መንፈሳዊ ጥንካሬ ለኛም ያድለን።
እውነትክን ነው ከኃዘኑ ብዛት የተነሣ ነፍሳችን የመከራ ዜናን ለምዳዋለች....!!!

ወንድሞቻችን የተሰውበትን ዕለት አስበህ መጻፍህ በጣም ደስ ይላል። እግዚአብሔር ይስጥህ።