Friday, May 27, 2016

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት?

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊነት በመወዳደር ላይ ይገኛል። በአገሩ የከለከለውን በነጻ ውድድር ሥልጣን መያዝን በመለማድ ላይ ነው። አያሌ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ድርጅቶች ምርጫውን አምርረው ሲቃወሙ የኢትዮጵያን መንግሥት ጨምሮ ብዙ ወዳጆቹና የዓላመው ደጋፊዎች ደግሞ በብርቱ እየደገፉት ነው። በመካከል ላይ ያሉ “ምናለበት” የሚሉ ኢትዮጵያውያን ድምጾችም ይሰማሉ።
ዶክተሩ የዓለማቀፉን ኅብረተሰብ የሥልጣን ማማ ለመቆናጠጥ የሚያደርገው ጥረት ሁል ጊዜም የምፈራውን አንድ እውነታ በድጋሚ እንዳነሣው አስገደደኝ። ይህም በጥቂቶች ለጥቂቶች የተመሠረተው የኢትዮጵያ መንግሥት የልፋቱን ውጤት እና የዕቅዱን ግብ መምታት የመቻሉ እውነታ ነው። በአገር ውስጥ ከመሬት ጀምሮ ማንኛውንም የኢኮኖሚ ምንጭ በቁጥጥሩ ሥር አውሏል። ወታደሩ፣ ደኅንነቱ፣ ፖሊሱና በጠቅላላው ቢሮክራሲው በእጁ ነው። አሁን ደግሞ “ዕውቀት እና ችሎታ” የሚባለውን ትልቅ የለውጥ መሠረት ለመቆናጠጥ ያደርግ የነበረው ሥር የሰደደ ቅሰጣ ተሳክቶለታል ማለት ነው። በመጠኑ ለማብራራት ልሞክር።

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ታሪክ ውስጥ ዕውቀት እና ጥበብን ከሰለጠነው ምዕራባዊ ዓለም ወደ አገራችን ለማስገባት በተደረገው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሀብት መጠናቸውና ዘራቸው ሳይታይ ሁሉም የዕውቀቱ ተካፋይ እንዲሆኑ በብዙ እንደተጣረ የትምህርት ታሪክ ምሁራን ይመሰክራሉ። በግርማዊ ቀ/ኃሥላሴ የትምህርት ፖሊሲ ተጠቃሚ ከሆኑት እና በመላው ዓለም ተጉዘው ዕውቀት ከሸመቱት የመጀመሪያው ትውልድ ወገኖቻችን መካከል ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት ከድሃው ሕብረተሰብ መካከል የተገኙ መሆናቸው የሚያሳየው ዕውቀት በማደሉ ሒደት ልዩነት እንዳልተደረገ ነው።
በወታደራዊው ደርግ ዘመንም ቢሆን ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል፣ ከሁሉም ጎሳና ብሔረሰብ የወጡ ዜጎች አገሪቱ ማቅረብ የቻለችውን ዕውቀት ሁሉ ሲገበዩ ኖረዋል። ይህም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስለሆነ ማብራሪያ አያሻውም።
ኢሕአዴግ (ወያኔ) ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ያደረገው መሠረታዊ አብዮት የዕውቀት ምንጩን መቆጣጠር ወይም ማፈራረስና በራሱ አርአያና አምሳል መፍጠር፣ እንዲሁም ዕውቀት በሚፈልገው መጠን ማደል ብቻ ነው። ይህ በአብዛኛው ዜጋ ላይ የታወጀው የማደንቆር ታሪካዊ በደል የትምህርት ጥራቱን በማንኮታኮት ለፖለቲካዊ ዓላማቸው የሚመጥን ዜጋ በመፍጠር ላይ ብቻ ያተኮረ የትምሀርት ፖሊሲ ሲከተሉ ቆይተዋል።
በሌላው በኩል ግን “የራሴ ወገን ነው” የሚሉትን ክፍል ዓለም ያፈራችውን ዕውቀት እንዲያገኝ በአገር ውስጥም በውጪ አገርም ባሉ ታላላቅ የዕውቀት መገብያ ቦታዎች በመላክ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በማስተማርም ላይ ይገኛሉ። በአሜሪካ እና እንግሊዝ፣ በደቡብ ኮሪያ እና ቻይና እንዲሁም በሌሎች የአውሮፓ ዩኒሸርሲቲዎች የሚማሩት የእነርሱ ሰዎች ቁጥር ቀላል ካለመሆኑም በላይ ብዙዎቹም ትምህርታቸውን ፈጽመው ቁልፍ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ድርጅት ቦታዎችን ሊይዙላቸው ችለዋል። ከነዚህ ቦታዎች መካከልም የመንግሥት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የተ.መ.ድ ክፍት የሥራ ቦታዎች እና ሥልጣኖች ተጠቃሽ ናቸው።
በንግዱ እና በቢሮክራሲው ላይ ያላቸውን የበላይነት እንዳረጋገጡት ሁሉ በዕውቀትም ላይ የበላይነት ካላቸው ሌላው ዜጋ ባሪያቸው እና ተገዢያቸው ሆኖ ለምዕተ ዓመታት የሚቀጥልበትን ትልቅ በር ከፈቱ ማለት ነው። ከ1960ዎቹ ማግስት ጀምሮ ነጻነታቸውን ያወጁ የአፍሪካ አገራት ከኢኮኖሚያዊ እና ከዕውቀታዊው ባርነት ነጻ ባለመውጣታቸው ብዙሃኑ ዜጋቸው በላዕላይ ሲታይ ነጻ ነገር ግን በተግባር ሲታይ ቅኝ ተገዢ ሆኖ እንደቀጠለው ሁሉ ኢትዮጵያም ይህ ዕጣ ፈንታ የሚወድቅባት ይመስላል።
በዘመነ ፋሺስት ጣሊያን ነጻነት ከተመለሰ በኋላ፤ ንጉሡ የቢሮክራሲውን ኃላፊነት ለመስጠት ልምዱ ያላቸው ሆነው የተገኙትን «ባንዳዎች» ለመሾም የተገደዱት አንድም በዚህ ምክንያት (ሌላው ለአገሩ ነጻነት በዱር በገደል ሲዋደቅ እነርሱ ከነጭ ገዢዋቸው የለቃቀሟትን ትራፊ ዕውቀት በመያዛቸው) እንደሆነ በሰፊው ተጽፏል፣ ተነግሯል። ወደፊት በአገራችን ነጻነት እና እኩልነት የሚመለስበት ዕድል ሲመጣ፣ ዛሬ የዕውቀቱን ማማ የጨበጠ (በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በአድልዎ ባገኙት ዕድል የተማሩት) የዚህ የጥቂቶች መንግሥት አባላት በችሎታቸው እየተመረጡ በሌላው ሰው ትከሻ ላይ የሚፈናጠጡበት ሰፊ ዕድል ያገኛሉ። 
ዶ/ር ቴዎድሮስ ይህንን ዓለምአቀፍ ሥልጣን ለመያዝ ሲወዳደር እርሱ ያገኘውን የዕውቀት ዕድል የዘጋባቸው ዜጎቻችን፣ በፓርቲው ወታደሮች ጥይት በመንገድ ላይ ደማቸው ደመ ከልብ የሆኑት ዜጎች ፊት፣ በእርሱ መንግሥት ፖሊሲ መሬታቸውን አጥተው ጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ገበሬ ወገኖቻችን ዕንባ፣ የዕውቀትን ደጃፍ እንዳያዩ ቤተሰባቸው የተበተነባቸው ለጋ ሕጻናት ፊት ይታየኛል። 

1 comment:

Endxis said...

የሚያም ሀቅ