Wednesday, June 1, 2016

ሰውየው ምን እያደረጉ ነው?

ሰሞኑን ማኅበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ በሚያሰደንቅ ሁናቴ ተጀምሮ መፈጸሙን ሲዘገብ በፎቶም በቪዲዮም ተከታትለናል። ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ በእምነት የሚመስሉንም፣ የማይመስሉንም ብዙ ወገኖች ለሰዓታት ተሰልፈው ማየታቸውን ተመልክተናል። "ምነው በኖርኩና የዚህ በረከት ተካፋይ በሆንኩ" የሚያሰኝ ታላቅ ተግባር ነበር። በተለይም ዐውደ ርእዩ ከውጥኑ ሊካሔድ ከነበረበት የዐቢይ ጾም እኩሌታ ወደዚህ የዞረው በደረሰው የመታገድ ችግር መሆኑ በተመልካቹ ዘንድ ጉጉት ሊፈጥር የሚችል ይመስለኛል። መታገዱ ከፈጠረው የምእመናን መከፋት ጋር ተያይዞ ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ መውጣቱ፣ ማኅበሩም ስሙንና ዝናውን እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ እና ደረጃውን የጠበቀ ዝግጅት ማቅረቡ ታሪካዊ ሊያሰኘው የሚችል ነው።

በዚህ ዐውደ ርእይ ላይ የተነሡ እጅግ ብዙ ፎቶግራፎችን በጉጉት ስንመለከት ቆይተን የመጨረሻ መጨረሻ የአቦይ ስብሐት ነጋ ፎቶ ሲመጣ ወዲያው የፌስቡክ መነጋገሪያ ለመሆን ችሏል።  ዘሐበሻ ድረገጽ “አማራን እና ኦርቶዶክስ እምነትን እንዳያንሰራራ አከርካሪውን መትተነዋል" ያለው ስብሃት ነጋ በማህበረቅዱሳን ዐውደ ርዕይ ላይ መጽሐፍ ገላጭ ሆኖ ታይቷል:” ያለውን ብዙዎች ድጋሚ “ሼር” አድርገውታል። ማኅበረ ቅዱሳንን በወያኔ ወዳጅነት ለመክሰስ የሚዳዳቸው ብዙ አካላትን ከ”ሼር”አድራጊዎቹ መካከል ማየቴ “ቁምነገር ያገኛችሁ መስሏችኋል” ማለት የሚገባ እንደሆነ ተሰምቶኛል።
መንፈሳዊ ዐውደ ርእይን ከፍ ባለና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በማዘጋጀት ረገድ ማ/ቅዱሳን ትልቅ ተሞክሮ አለው። (ዐውደ ርእይ የሚለው ቃል የተፈጠረው በማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን ላስታውስ፤ ለ1994ዓ.ም ኤግዚቢሽን ወቅት):: በአገር ቤት በዝግጅቱ ለመካፈል ዕድል ያገኘሁባቸው የ1989 እና የ1992 ዓ.ም ዐውደ ርእዮችን ጨምሮ በውጪ አገር የተዘጋጁትን የተለያዩ ዐውደ ርእዮች ለመጎብኘት የሚመጣው ሰው ስብጥር የተለያየ መሆኑን ተመልክቻለሁ። በቀናነት ትምህርት ለመቅሰም የሚመጣው እንዳለ ሁሉ የራሱን ግምገማ ወስዶ ለሌላ ዓላማ ግብዓት ሊያደርገው አስቦ የሚመጣው የዚያኑ ያህል አለ። የ1989 ዓ.ምሕረቱ ገና የመጀመሪያ እና ሐሳቡም ራሱ በሕዝብ ዘንድ ያልተለመደ እንደመሆኑ በሕዝብ ቁጥር እና በስብጥር ደረጃ እንደኋለኞቹ አይደለም። የ1992ቱ ግን ደረጃውን የጠበቀ እና ከተርታ ዜጋ እስከ መንግሥት ባለሥልጣናት ድረስ የጎበኙት እንደነበር አስታውሳለሁ። ከነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ደግሞ አቦይ ስብሐት አንዱ ነበሩ።
አቦይ ስብሐት ለቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ቅርበት ያላቸው እና ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸውን ጠንቅቄ አውቃለኹ። በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ በግልጽ ትችትየሚያቀርቡ ዋነኛው የሕወሐት ሰው መሆናቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል በሙሉ የሚገነዘበው ነገር ነው። ከዚህ የተነሣም ሰውየው የማ/ቅዱሳንን ዐውደ ርእይ ማየታቸው የሚጠበቅ ነው። በፎቶው ላይ እንደሚታየው ከጉብኝታቸው በኋላ አስተያየት ለመስጠት ተቀምጠዋል ማለት ነው። ገልጠው የሚታየው ባሕር መዝገብ የሐሳብ መስጫ ደብተር እንጂ መጽሐፍ አይደለም።

በርግጥ ለዲፕሎማሲው ሲሉ ጥሩ ጥሩ ነገር ሊጽፉ ወይም ሊናገሩ እንደሚችሉ ብጠብቅም ፓርቲያቸው ቤተ ክርስቲያን ላይ ያለውን አቋም ጠንቅቆ ለተረዳ ሰው ግን የተለየ በጎ ምላሽ ወይም የልብ መሰበር ሊጠብቅ አይችልም።     

2 comments:

birku belachew said...

አቦይ ስብሀት ነጋ የኢ.ኦ.ተ.ቤ/ክ ለማደከምና ለማጥፋት ታጥቀው ከተነሱ የጥፋት ልጆች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፤ አልተሳካለትም እንጂ፡፡ ትግሉ ከማን ጋር እንደሆነ እስከ አሁን ድረስ አልገባውም፡፡ ባለፈው ፹፫ኛ ዓመቱን አክብሮአል፤ የሰው ልጅ ዕድሜ ፸ ቢበዛ ፹ ነው፣ ስብሀት ግን ጣሪያውን አልፏል፣ ማስተዋል ቢችል ዕድሜ ለንስሐ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ዛሬም በስከ እርጅና ዘመኑ የለመደውን የክፋት የተንኮል ስራ ቀጥሎበታል፡፡ በእርጅና ዘመኑ እንኳን መለወጥ ያልቻለ ክፉ ሰው፡፡

Anonymous said...

“አማራን እና ኦርቶዶክስ እምነትን እንዳያንሰራራ አከርካሪውን መትተነዋል" ያለው ስብሃት ነጋ በማህበረቅዱሳን ዐውደ ርዕይ ላይ መጽሐፍ ገላጭ ሆኖ ታይቷል:” May be he is coming to see አከርካሪው broken or not....