Wednesday, August 3, 2016

"ከመላው አገር ወዳድ ክርስቲያኖች ለተጋሩ (ትግሬ) የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በሙሉ የቀረበ የወገንህን፣ አገርህን እና ሃይማኖትህን አድን ወቅታዊ ጥሪ!!!!!!"

 “አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፤ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ … ለድሀና ለምስኪን ፍረድ።” (ምሳሌ 31፡8-9)
መነሻ
(READ IN PDF):- ትግራይ የኢትዮጵያ አገራችን የክርስትና/እስልምና እምነቶች እና የሥነ መንግሥት አስኳል ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ ክልል ነው። የአገራችን ኪነ እምነትም ሆነ ኪነ ሕንጻ፣ ኪነ ዜማም ሆነ ኪነ መንግሥት ማማ ትግራይ ነው። ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ማሰብ እንደማይቻለው ሁሉ ኢትዮጵያን ከትግራይ ነጥሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የእምነትና የአገር ማማና ምሦሦ የሆነ ሕዝብና ክልል በዘመናችን ታሪካዊ ጥያቄ ቀርቦለት ይገኛል።
ታሪካዊ ጥያቄው አገራችን ኢትዮጵያ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥም የሰላምና መረጋጋት እጦት በማየሉ የአገሪቱ ሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ እጅግ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ዜጎች በጅምላ የሚገደሉበትን እና በጅምላ ወደማሰቃያ እስር ቤቶች የሚጋዙበትን መከራ የተመለከተ ነው። ከታላቁ የትግራይ ክልል የበቀለው እና ላለፉት 25 ዓመታት መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የሕወሐት ቡድን የሚመራው ፓርቲ እና መንግሥት ለዚህ ቀውስ ዋነኛው ምክንያት መሆኑ ለታሪካዊው ትግራይ ፈተና ሆኖ ቀርቧል።
ይህ ፓርቲና መንግሥት ላለፉት 25 ዓመታት የዘረጋው የአፈና እና የሰቆቃ ሰንሰለት ከሕዝቡ አቅም በላይ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች አመጽ በመቀስቀስ ላይ ከመሆኑም ባሻገር አመፁ የአገሪቱን ሕልውና የሚፈታተን ሊሆን እንደሚችል የብዙ ባለሙያዎች እና ተመልካቾች ግምት ነው። ስለዚህም አገራችን ልትወጣው የማትችለው ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ በፊት ሕወሐት በስሙ ለሚነግድበት የትግራይ ሕዝብ ጥሪ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ሐተታ
በርግጥ የተዋሕዶ እምነት ተከታዩን ብቻ ለይቶ ጥሪ ማድረግ ለምን አስፈለገ ሊባል ይችላል። አብዛኛው ሕዝብ ለሚከተለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ጥሪውን በቀጥታ ማቅረብ ያስፈለገበትን ምክንያት በጥቂቱ እንደሚከተለው መግለጽ ይቻላል።
1ኛ. ጉዳዩ ክርስቲያኑን ብቻ የሚመለከት ስለሆነ ወይም ሌላ እምነት የሚከተለው ኢትዮጵያዊ ጉዳዩ ስለማይመለከተው ሳይሆን ጥሪውን ለማስተላለፍ የተሰባሰቡት ወገኖች የተሰበሰቡበት ዐውድ ሃይማኖት በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በመሆኑ ጥሪውን ለእምነት አጋሮቻቸው ማቅረቡ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣
2ኛ. በ1999 ዓ.ም የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት እንደሚያመለከትው ከጠቅላላው የትግራይ ሕዝብ መካከል 95.6 በመቶው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ በመሆኑ እና የዚህ ምእመን ውሳኔ በሕወሐት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ እና የተዋሕዶ እምነት ተከታዩ የትግራይ ሕዝብ ታቦተ ጽዮንን ጨምሮ በታሪክ የተሸከመው እምነቱንና አገሩን የመጠበቅ ታሪካዊ አደራ እንዳለበት ለማስታወስ፣
3ኛ. አገራችን አሁን ከገባችበት ቀውስ አንጻር ክርስቲያኑ የትግራይ ሕዝብ ሃይማኖቱ የሚያዘውን ሃይማኖታዊ ግዴታ በፍፁም መንፈሳዊነት ቢፈጽም አገሩን፣ ሃይማኖቱን እና ራሱን ከታላቅ አደጋ ሊያድን እንደሚችል ፍፁም እምነት በመኖሩ፣
4ኛ. በዘር ላይ በተመሠረተው እና ለመግባባት እና ለመወያየት ዕድል ሊከፍት ባልቻለው የዘር ፖለቲካ ግራ የተጋባው ሕዝባችን ተስፋ ወደ መቁረጥ በመድረሱ እና በቀቢጸ ተስፋ ሊወስድ የሚችለው ርምጃ ነገ ልንቀለብሰው የማንችለው አዘቅት ውስጥ እንዳይጥለን በማስጋቱ ለትግራይ ክርስቲያን ወገናችን ቀጥታ የአገርህን እና ሃይማኖትህን አድን ጥሪ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ምን ይላል?
ለትግራይ የተዋሕዶ ወገናችን ጥሪ ስናስተላልፍ ቅድስት ክርስቲያናችን ከቅዱሳት መጻሕፍት ባገኘችውና ዘወትር በምታስተምረው ትምህርት ላይ ተመርኩዘን ነው። ከብዙው በጥቂቱ የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች እንመልከት።
1ኛ. እግዚአብሔር ሁላችንንም በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮናል። ሁላችንም የእጁ ሥራዎች ነን። ለአያሌ ዘመን በአንድ አምላክ እምነት የኖርን ሕዝቦች ነን። በኋለኛውም ዘመን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን በደሙ ተዋጅተን ልጅነትን ያገኘነው የአንድም የሐዋርያ ደም ሳናፈስ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊዎች በሙሉ ይመሰክራሉ።መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን በሞቱ የሞትን ማሠሪያ ሲፈታልን እርሱ አባታችን ሁላችንም ደግሞ ወንድም እና እህት ሆነናል። አባታችን እግዚአብሔር እናታችን ቤተ ክርስቲያን ብለን ለክብር በጠራን አምላክ ፈቃድ የአንድ አምላክ ልጆች ተብለናል።
2ኛ. ክርስትና ለተለየ ዘር፣ ለተለየ ጎሳ እና ነገድ የተሰጠ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ እና ወገን ክርስቲያን ይሆን ዘንድ የተጠራበት ሰማያዊ ቤተሰብ እንደመሆኑ ቋንቋ፣ የትውልድ ሐረግና እና መኖሪያ አካባቢ በሥላሴ አርአያ የተፈጠረው የሰው ልጅ መለያያ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ቅዱስ ጳውሎስ «አልቦ በዝንቱ አይሁዳዊ፣ ወአልቦ አረማዊ፣ ወአልቦ ነባሪ፣ አልቦ አግዓዚ፣ አልቦ ተባዕት ወአልቦ አንስት፤ ዳእሙ ኩልክሙ አሐዱ በኢየሱስ ክርስቶስ። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።» ሲል ለሰብዐ ገላትያ (3፡28) እንደጻፈላቸው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም በሰው ልጅ አንድነት ታምናለች ታስተምራለች። ከዚህ ውጪ የዚህ ብሔረሰብ፣ የዚህ ብሔር፣ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ እያሉ ሰውን ማቅረብና ማራቅ ከመንግሥተ እግዚአብሔር እና ከክርስትና ትምህርት መለየት ነው።
3ኛ. ኦርቶዶክሳዊነት ከድንበር እና ከክልል በላይ ነው። ከአራቱ የቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች መካከል ማለትም «ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፣ ቅድስት ናት፣ ሐዋርያዊት ናት፣ ዓለማቀዊት ወይም የሁሉ እና በሁሉ ያለች ናት» ከሚለው ውስጥ ዓለማቀፋዊነት (የሁሉ እና በሁሉ ያለች) የሚለው ነጥብ ክርስትና በዜግነት ብቻ ያልተከለለ መሆኑን ያሳየናል። ሐዋርያዊት ስለሆነችም እንደ ሐዋርያት ትምህርት ድሃውንና ባለጸጋውን፣ ገዢውንና ምንዝሩን፣ የሰማዩንና የምድሩን አንድ አድርጋ የምታስተዳድር፣ በሰዎች መካከል ልዩነትና ድንበር የማታበጅ ቤተ ክርስቲያን ናት።
4ኛ. ቤተ ክርስቲያናችን የዜግነት ድንበር የማያግዳት «የሁሉ እና በሁሉ ያለች» ብትሆንም ኢትዮጵያ ደግሞ በአምላክ ዘንድ የተወደደች፣ እንደ ሕጉ እና እንደ ተስፋ ቃሉ የኖረች፣ በቅዱሳን ኪዳተ እግር የተባረከች፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ የበዙ ቅዱሳንን/ ቅዱሳትን ያፈራች ቅድስት አገራችን ናትና እምነታችንን ከአገራችን፤ አገራችንን ከእምነታችን ለይተን አንመለከትም። በእምነታችን ላይ የሚመጣ የአገራችን አደጋ እንደሆነ፤ በአገራችን ላይ የሚመጣ አደጋ ደግሞ የእምነታችን አደጋ እንደሆነ አበው አስተምረውናል። «ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት» አድርግልን ብለው በጸሎት እንደጠበቋት ሁሉ የግዱ ቀን ሲመጣም ስለ አገራቸውና ስለ እምነታቸው ሰማዕትነት ለመቀበል ታቦታቸውን እና መስቀላቸውን ይዘው ከጦር አውድማ ውለው ውድ ሕይታቸውንም በሰማዕትነት እንደከፈሉት ሁሉ ለአገራችን ሰላምና አንድነት እኛነታችንን መስጠት እንዳለብን እንገነዘባለን።   
5ኛ. ሁሉንም ከምድር አፈር ያበጀ፣ አእምሮውን ለብዎውን ያድላቸው ዘንድ በእስትንፋሱ ያጸናቸው አምላክ እርሱ ለማንም እንደማያዳላ ቅዱስ ጴጥሮስ «አማነ ርኢኩ ከመ ኢያደሉ እግዚአብሔር ለገጽ በኩሉ አሕዛብ። እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያደላ በውነት አየሁ» (የሐዋ. 10፡34፤ ዘዳ 10፡ 17፤ 1ሳሙ 16፡7፤ ሮሜ 2፡11) ሲል ያስተማረውን አንገነዘባለን።
6ኛ. ይሁን እንጂ በስመ ክርስቲያን የምንጠራ ኦርቶዶክሳውያን ከዚህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ርቀን፣ ይልቁንም በአሕዛብ እንኳን የሌለ መለያየት በመፍጠር፣ ሰዎችን በቋንቋቸው እና በዘር ሐረጋቸው በመውደድና በመጥላትፀ በመጥቀምና በመጉዳት ለአገራችንም ለሃይማኖታችንም ትልቅ የመሰናክል ድንጋይ አስቀምጠናል። ያለፈውን ዘመን ብንተወው እንኳን በዘመናችን ብቻ የመለየየታችን እና የመጠላላታችን ውጤት አገራችንን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥበት ድንበር ላይ አድርሶናል። እንደ ችግሩ ምንጭ ሁሉ መፍትሔውም ከሁሉም የሚጠበቅ ቢሆንም ለታሪካዊው የትግራይ ሕዝብ ግን እነሆ ፈታኝ ጥያቄ ሆኖ ቀርቦለታል።  

በዚህም መሠረት፡-
1ኛ. የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለይቶ የሚቀርበት አስከፊ የታሪክ አጋጣሚ እየተከሰተ መሆኑን በጥሙና እንዲገነዘብ፣
2ኛ. ላለፉት ሁለት እና ሦስት ሺህ ዓመታት አብሮ የኖረው ሕዝብ እና የሃይማኖት ቤተሰብ ከኤርትራ ጋር እንደተፈጠረው ያለ ፖለቲካዊ መለያየት እና መከፋፈል፣ እንዲሁም ከሌላው የሃይማኖት ወገኑ ተነጥሎ የመቅረት ዕዳ ሊወድቅበት እንደደረሰ እንዲያስታውስ፣
3ኛ. ለዚህም ክርስቲያኑ ተጋሩ በዋነኝነት የመከፋፈሉን ተግባር እየሠራ ያለውና በትግራይ ስም የሚነግደው የሕወሐት ቡድን መሆኑን አውቆ በደስታውም ይሁን በሐዘኑ ከእርሱ ከማይለየው ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ እንዲቆም፣
4ኛ. በመንፈሳዊ እና በማኅበራዊ ሕይወቱ ዘወትር አብሮት ያለውን የቀሪውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን የለትተዕለት ሰቆቃ፣ እስር፣ እንግልት፣ ከመሬትና ንብረት መፈናቀል፣ ግድያ እና ስደት የርሱም (የትግራይ ወገኑም) ሰቆቃ፣ እስር፣ እንግልት፣ከመሬትና ንብረት መፈናቀል፣ ግድያ እና ስደት መሆኑን አምኖ ለወገኑ ድምጹን እንዲያሰማ፣
5ኛ. አገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ነጥብ በማስቆጠር ይህንን የመከራ ዘመን ለማራዘም ደፋ ቀና የሚለውን ፓርቲ ኢ-ሃይማኖታዊ፣ ኢ-ባህላዊ እና ኢ-ኢትዮጵያዊ ጥሪ አልቀበልም በማለት ለነገው የትግራይ ተተኪ ትውልድ ግፍ እና ቂም እንዳይተርፍ እንዲያደርግ፣
6ኛ. ከሕወሐት ጋር በማበር የፓርቲውን የሰቆቃ ተግባር ከሚባርኩት በትግራይ ምእመን ስም በጵጵስና፣ በምንኩስና እና በክህነት ባለሥልጣንነት ከሚነግዱት ትግራዋዮች እንዲለይና እና ዘረኝነትን፣ ግፈኝነትን፣ ደም ማፍሰስን ከሚጠየፈው ከአማናዊው የተዋሕዶ ትምህርት ጎን በመቆም ቀሪ ኢትዮጵያዊ ወገኑን እንዲታደግ፣
7ኛ. የትግራዩ ወገናችን ሌላውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን ሊያጠፋ እንደመጣ ጠላት አድርገው የሚነግሩትን የአገርና የሃይማኖት ተቃራኒዎች አልሰማም በማለት በቤቱ፣ ከራሱ ወንድሞች እና እህቶች ጋር በሚያውቀውና በሚረዳው አግባብ እንዲወያይ እና መፍትሔ እንዲያበጅ፣
8ኛ. በመላው አገሪቱ በተለይም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በየቀኑ የሚፈሰውን የንፁሐን ደም እንዲያስቆም፣
9ኛ. ማንኛውም ዜጋ ሊያገኘው የሚገባውን መብት፤ (ለምሳሌ በታመሙ ጊዜ ሕክምና የማግኘትን መብት)፤ ለተከለከሉ ወገኖች ጠበቃ እንዲሆን መጠየቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እነሆ ጥሪውን አቅርበናል።
በፈሪሀ እግዚአብሔር ተቃኝቶ ለኖረው ለትግራይ ሕዝብ በሌላው ሕዝብ መከራ፣ ሞትና ስደት በመበልፀግ ላይ ያለ ቡድን ደጋፊ እና አጋር መስሎ እንደመታየት ልብን የሚያደማ ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን። በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት የሚያስፀይፍ በደል የሚፈጽሙትን ሰዎች የሚቃወሙ አያሌ ትግራዋዮች (ትግሬዎች) እንዳሉ ግልጽ ቢሆንም የእነርሱ ዝምታ ክፉዎችን የልብ ልብ ሰጣቸው እንጂ ከድርጊታቸው ስላልመለሳቸው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መጠየቅ ግድ ብሏል።  
ይህ ጥያቄ የትግራይ ሕዝብ የፈጸመው የተለየ ዕዳና በደል ስላለበት የቀረበ ጥሪ ሳይሆን እንደ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ኃላፊነቱ ሊወጣ የሚችለው ሚና ከፍ ያለ እንደመሆኑ ሳይደርቅ በርጥቡ፣ ሳይርቅ በቅርቡ መፍትሔ ይፈልግ ዘንድ ለማበከር ነው። ጌታም እንዳስተማረን «ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።» (የሉቃስ ወንጌል 12፥48) እንዲል። ታቦተ ጽዮን በአክሱም ያረፈቸው እና ለአክሱማውያን የጠባቂነቱን ኃላፊነት እግዚአብሔር ባወቀ የተሰጠው ያለ ነገር አይደለም። የንጉሥ ካሌብ አጽም ያረፈበት ምድር፣ ተሰዓቱ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ የፈጸሙበት፣ ቅዱስ ያሬድ የበቀለበት ምድር ሕዝብ ለሌላው ወገኑ ደራሽ፣ የኃዘኑ ተካፋይ እንዲሆን መጠበቅ ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይሆንም።
ስለዚህም ከምሥራቅ የኦጋዴን በረሃዎች እስከ ጋምቤላ፣ ከወልቃይት፣ ጠገዴና አፋር እስከ ኦሮሚያ ከተማና ገጠሮች ያለው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ሰቆቃ የሚገዳቸው እና ዕንባውን ሊያብሱለት የሚሹ፣ የተቃጣበትን ከባድ ጦር የሚያረግቡለት የትግራይ ወገኖቹን መፈለጉ ተገቢ የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።  
ይህ በኢትዮጵያዊነት እና በተዋሕዶ ወገንተኝነት የቀረበ ጥሪ በጊዜያዊው የፖለቲካ ፀጉር ስንጠቃ ሳይመዘን በጎ ምላሽ እንዲያገኝ ምኞታችን ነው። በተለይም ቃለ እግዚአብሔርን በየአጥቢያቸው በመስማት ተኮትኩተው በማደግ ላይ ያሉ ወጣት የትግራይ ወንድሞች እና እህቶች ዘመኑ ያመጣው የመለያየት አባዜ ሰለባ ሳይሆኑ በአገራዊ አንድነት እና በሃይማኖታዊ ዜግነት ተጠልለው ራሳቸውንም ወገናቸውን ወደ አንድነት የሚመሩ የፍቅር መልእክተኞች እና መከራ በመቀበል ላይ ላለው ሌላው ወገናቸው የሚቆረቆሩ እንደሚሆኑ ተስፋ አለን።                             
በመጨረሻም፡- እግዚአብሔር በሰጠን ጊዜ ተጠቅመን ይህንን ሳናደርግ ብንቀር ግን መዘዙ የከፋ መሆኑን የሚያሳዩ የምጥ ጣር መጀመሪያ ምልክቶች መታየት መጀመራቸውን ሳይጠቅሱ ማለፍ የዚህን ጽሑፍ መልእክት ማጨንገፍ ይሆናል። የትግራይ ሕዝብ ያለበደሉ እና ያለ ኃጢአቱ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ደም ተቃብቶ፣ በጠላትነት ተፈርጆ፣ አንዳንድ ኅሊና ቢሶች እንደሚያደርጉትም ከትግራይ በመፈጠሩ ብቻ ከዘመኑ አጥፊዎች ጋር ተደምሮ የጥቃታቸው ዒላማ ሆኖ ሊታይ እንደሚችል ምልክቶቹ በይፋ ይታያሉ። ከአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን እስከ ተሰዓቱ ቅዱሳን፣ ጻድቃን ከሚባሉት ከ500ዎቹ ቅዱሳን እስከ አባ ሰላማ መተርጉም፣ ከአቡነ አረጋዊ እስከ አባ ገሪማ ጻድቅ፣ ከቅዱስ ያሬድ እስከ አቡነ ተ/ሃይማኖት በበረከታቸው የጎበኙት ሕዝብ እና ምድር ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በጥላቻ መጋረጃ ተሸፍኖ እንዳይቀር በእጅጉ ያሰጋል።
ስለዚህም በጎ ኅሊና ያላቸው የትግራይ ወገኖቻንን በሙሉ መልእክቱን በጥሙና ተመልክተው እንዲወያዩበት፤ በአገር ሽማግሌ፣ በተከበሩ አባቶች እና እናቶች ምክር ኢትዮጵያውያን በዘርና በቋንቋቸው እየተለያዩ የሚጠፋፉበትን ክፉ መርዝ እንዲያመክኑ፣ ለዚህም የትግራይ አንጋፋዎች የሰላም መልእክተኞች እንዲሆኑ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ይህ መልእክት ለክርስቲያኑ በይፋ የቀረበ ቢሆንም በእምነት አንድ ባንሆን በዜግነት አንድ የሆንን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያለ እምነት እና ብሔረሰብ ልዩነት ለሰላም ጥሪ ለማድረግ የምንነሣበት እንዲሆን እንመኛለን። ከልባችን መልካም ነገር ለማድረግ ብንነሣ ደግሞ እሳተ መዓቱን በምሕረት ውኃው የሚያቀዘቅዝ አምላክ ለሰላም አልዘጋጅ የሚል ድንጋይ ልባችንን በሰላም ልብ ቀይሮ ሰላማዊ ልብ እንደሚሰጠን ምሉዕ እምነት አለን።  

እግዚአብሔር አምላካችን አገራችንን እና ሕዝባችንን ከሚታየውና ከሚሰማው ክፉ ነገር ሁሉ ይሰውርልን፣
         
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ወገኖቻችሁ ከመላው ዓለም


12 comments:

B said...

ውድ ወንድማችን በዚህ በምጥ፣ ስዓት እንዲህ አይነቱን ወቅታዊ ጥያቄ ይዛችሁ ብቅ በማለታችሁ እጅግ በጣም እናመሰግናለን። እግዚአብሔር የሚወደውም እንዲህ አይነቱን፣ የወገን ደራሽነቱን ነው። እውነትን ይዘናልና አይጥለንም። ለወገኖቻችን ጥሪውን እናስተላልፋለን። ወያኔዎቸ በተለይ ቅልቦቹ፣ በተለያዬ ስም እየገቡ ይኸን ጥሪአችሁን ፍሬ አልባ ለማድረግ ይሞክራሉ። በዚህ ተስፋ ሳትቆርጡ፣ ወቅቱን የጠበቁ ጥሪዎችን ብታስተላልፉ የነጻነት አዬር በአገራችን የምንተነፍስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

Bini N said...

ጽሁፉን በማይሆን እና ጻፍኩበት ካለበት አላማ ውጪ በሆነ ጥቅስ ነው የጀመረው ፡- ““አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፤ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ” …. የትግራይ ህዝብ ዲዳ ስለሆነ ሊናገርለት እንዲሁም ተስፋ ስለሌለው ሊፋረድለት አስቦ መጀመሩን በጥቅሱ ነግሮናል….. ግን የትግራይ ህዝብ ብሶቱን እና መጨቆኑን የሚናገሩለት ብዙዎች አሉ በሶሻል ሚዲያውም ሆነ በፖለቲካውም ግን ኤፍሬም እነሱ አልታዩትም ፡፡ይህ አይገርምም በዙዎች ጥቅስን በምን አግባብ መጥቅስ አንዳለባቸው ስለማያቁት አይገርመኝም፡፡

“አገራችን አሁን ከገባችበት ቀውስ አንጻር ክርስቲያኑ የትግራይ ሕዝብ ሃይማኖቱ የሚያዘውን ሃይማኖታዊ ግዴታ በፍፁም መንፈሳዊነት ቢፈጽም አገሩን፣ ሃይማኖቱን እና ራሱን ከታላቅ አደጋ ሊያድን እንደሚችል ፍፁም እምነት በመኖሩ “ …….. አገራችን አሁን የገባችበትን ቀውስ ለማዳን የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው እንዴ ሀላፊነት ያለበት ? “ራሱን ከታላቅ አደጋ ያድናል” ይህስ ምን ማለት ነው ? የትግራይ ህዝብ መንግስትን ተቃውሞ ሰልፍ ካልወጣ አደጋ እናደርስበታለን ወይም ታላቀ አደጋ ይደርስበታል እያለ ነው ? ለምንስ ታላቁን አደጋ የሚያደርሱትን “የትግራይን ህዝብ እና መንግስትን ለዩ! “ብሎ መምከር አልፈለገም ? የሚደርሰበትን ታላቅ አደጋ ነግሮ ከማስፈራራት ?

“የዘር ፖለቲካ ግራ የተጋባው ሕዝባችን ተስፋ ወደ መቁረጥ በመድረሱ እና በቀቢጸ ተስፋ ሊወስድ የሚችለው ርምጃ ነገ ልንቀለብሰው የማንችለው አዘቅት ውስጥ እንዳይጥለን” ፡፡ የዘር ፖለቲካውን ታድያ የትግራይ ህዝብ አመጣው እንዴ ? ቢያነብ እና ቢያውቅ ኖሮ የዘር ፖለቲካውን እንኳን የትግራይ ህዝብ ህወሀትም እንዳላመጣው ያውቅ ነበር ፡፡ ህዝቡ ተስፋ ሲቆርጥ በቀቢጸ ተስፋ አሁንም የትግራይ ህዝብ ላይ እርምጃ ሊወስድ ስለሚችል እራስህን እና ሀይማኖትህን (እቺ እንኴን ሽፋን ናት) አድን እያለው ነው ፡፡ አሁንም የሚወሰድ እርምጃ እንዳለ(እንደሚኖር እርግጠኛ ነው) እየነገረን ነው ግን ይህን እርምጃ ወሳጆች ላይ ስለሃይማኖትቸው ሲሉ ዘር ላይ የተመረኮዝ እርምጃ ለመውሰድ እንዳይሞክሩ ሊመክረን አልፈለገም…. ለማይቀረው እርምጃ ስትሉ ህውሀትን በመቃወም ነፍጥ አንሱ ትግሬዎች እያለ ነው …… እውን ኤፍሬም መንፈሳዊ ወይስ ……. ?


ለትግራይ ህዝብ ጥያቄ ያላቸውን አስተውሎ ለሚያነብ ሰው ጸሀፊውን ምን ያህል የዲያስፖራው የጸረ-ትግራይ ፖለቲካ ውስጡ እንደሰረጸ እና የትግራይ ህዝብ ዲያስፖራ ላይ እንዳለው ሳይሆን በኢትዮጵያው ውስጥ ከጉራጌው፣ከኦሮሞው፣ከአማራው….እና ከሌሎቹም ጋር ተዋልዶ እና አንድ ሆኖ አንደ ኢትዮጵያዊ እየኖረ እንደሆነ …. “መንግስትን እና የትግራይ ህዝብን አንድ አድርጎ ማየት “ የዲያስፖራው የማይረባ ፖለቲካ በማህበራዊ ሚዲያ መለቀቅ ከጀመረ ጀምሮ አንደ አዲስ የተቀሰቀሰ ነገር እንደሆነ እንዳልገባው ያስታውቃል ፡፡
ለትግራይ ህዝብ ጥያቄ ባለበት ላይ “የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለይቶ የሚቀርበት አስከፊ የታሪክ አጋጣሚ እየተከሰተ መሆኑን በጥሙና እንዲገነዘብ” ይላል ፡፡ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚለይበት ታሪክ አጋጣሚ ለምንድን ነው የሚፈጠረው ? የትግራይ ህዝብ እኮ ህውሀት ሳይኖር ለኢትዮጵያ የሞተ ህዝብ ነው …ህውሀት ቢወድቅ አንድ ድርጅት ተገረሰሰ እንጂ ለምን የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ይለያል ? ይህ ህወሀት እና የትግራይ ህዝብን አንድ ከማድረግ መንፈስ አንዲሁም ይህ መንገስት ከወደቀ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር አይቀጥልም እያሉ በሚያሥወሩ በህውሀት ካድሬዎች መንፈሰ የተቃኘ አመለካከት ነው፡፡ጸሀፊው የዚህ ክፉ አመለካከት ሰለባ ስለሆን የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ የሚለይበነት ታሪካዊ አጋጣሚ ቀርቧል እያል የውስጥ ምኞቱን ይገልጻል ፡፡ ግን የትግራይ ህዝብ መቼም ቢሆን ከኢትዮጵያ አይነጠልም ግለሰቦች ሊነጠሉ ይችሉ ይሆናል እንጂ፡፡

…… “ከኤርትራ ጋር እንደተፈጠረው ያለ ፖለቲካዊ መለያየት እና መከፋፈል፣ እንዲሁም ከሌላው የሃይማኖት ወገኑ ተነጥሎ የመቅረት ዕዳ ሊወድቅበት እንደደረሰ” …. እንግዲህ የኤፍሬም አሸቴን መሰሪነት እና ለትግራይ ህዝብ ያለውን ምኞት ቁልጭ አድርጎ የገለጸበት ዓረፍተነገር ናት፡፡ እንደ ኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ተነጥሎ የሚቀርበት ጊዜ ቀርቧል እያለን ነው፡፡ እንግዲህ ጎንደር ላይ ኢህአዴግን ተቃውሞ ሰልፍ መደረግ ፣ኦሮሚያ ላይ ላለፉት 8 ወራት ተቃውሞው በመበርታቱ እና በመንግስት ታጣቂዎች ግድያ መፈጸሙ የትግራይ ህዝብ እንደ ኤርትራ ተገነጥሎ የሚቀርበት ጊዜ መቅረቡን ለኤፍሬም አሳይቶታል፡፡በጣም ይገርማል እኔ እሱን ብሆን ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ዲሞክራሳዊ ለውጥ እንዲመጣ ጨረር የፈነጠቁ ሰለፎች መሆናቸውን አስብ ነበር እንጂ አንድ ብሔርን ወስጄ መገንጠያ ቀንህ ደርሷል እያልኩ ክፉ ምኞቴን አልገልጽም ነበር፡፡

ኤፍሬም የትግራይ ህዝብንና ህወሃትን አንድ አድጎ ጽፎ ክፉ ምኞቱንም ገልጾ ካበቀ በኋላ መለስ እያለ …. “በትግራይ ስም የሚነግደው የሕወሐት ቡድን መሆኑን አውቆ” እያለ ህወሀት በትግራይ ስም የሚነግድ እንጂ የትግራይ ህዝብ እንዳልሆነ ሊነግረን ይሞክራል ፡፡ “በትግራይ ስም የሚነግድው ህወሃት ነውና ጭፍን ጥላቻችሁን ከትግራይ ህዝብላ ላይ አንሱ” ብሎ የትግይ ህዝብ ላይ “ታላቅ አደጋ” ያደርሳሉ ያላቸውን ወገኖች ግን መንፈሳዊ ምክር ሊመክር አልሞከረም ፡፡ እንደውም በድህነት ፣በስደት እና በመልካም አስተዳደር እጦት የሚሰቃየውን የትግራይ ህዝብ እንደ መንግስት በመቁጠር .. “በመላው አገሪቱ በተለይም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በየቀኑ የሚፈሰውን የንፁሐን ደም እንዲያስቆም” የሚል ጥሪ አቅርቦለታል፡፡ በትግራይ ህዝብ ልዩ ፈቃድ ኦሮሚያ ውስጥ ሰው የሚገደል ይመስል የትግራይ ህዝብ እንዲያስቆም ጥሪ አስተላልፏል፡፡ኤፍሬም “በፈሪሀ እግዚአብሔር ተቃኝቶ የኖረ” እያለ የሚጣራውን ህዝብ በኦሮሚያ ግድያ ደስተኛ እንደሆነ አድጎ በማቅረብ እና እንዲያስቆም ጥሪ ማቅረብ የትግራይን ሙሉ ህዝብ እንደ መንግስት ከማየት ካለው የተሸዋረረ አመለካከት የመጣ ነው፡፡
“በሌላው ሕዝብ መከራ፣ ሞትና ስደት በመበልፀግ ላይ “ያለ ቡድን” ደጋፊ እና አጋር መስሎ እንደመታየት ልብን የሚያደማ ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን።” ይለናል ኤፍሬም በመጨረሻ ፣ ቡድን እንጂ የትግራይ ህዝብ መንግስት አለመሆኑን ገብቶታል ብሎም ደጋፊ መስሎ እንደመታየት በማለት ህዝቡ ደጋፊ አድጎ ያቀርበዋል እንጂ የትግራይ ህዝብም እንደ ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ በጭቆና ላይ ነው፡፡
አፋር የተቃውሞ ሰለፍ የለም፣ወላይታ ሰለፍ የለም፣ጉራጌ ላይ የተቃውሞ ሰለፍ የለም ፣ ይህ ማለት እነዚህ ህዝቦች ተጠቃሚ ሆነዋል ማለት አይደለም የትግራይንም ህዝብ ዝምታ በዚህ መልክ ነው ማየት ያለብን፡፡

በአጭሩ ከላይ ያለው የኤፍሬም ጽሁፍ በጭፍን የትግራዋይን ጥላቻ እና ትግራይን የኢትዮጵያ አካል አድርጎ አለማያት (ሌላ ሀገር አድርጎ የማየት) የጠሽ ዲያስፖራ ፖለቲካ የተቃኘ ፣ከላይ መንፈሳዊ ውስጡ ግን ንቀት እና ህዝብን መለያየት ዓላማ ያነገበ ጽሁፍ ነው፡፡

Anonymous said...

I am orthodox Ethiopian, but to whom the written pieces has been addressed make me annoyed.However, i believe the existence of challenges in Ethiopia.

Anonymous said...

ዲ/ን መልእክትህ በጣም ልብ የሚነካ ነው። እኔ ከተጋሩ ቤተሰብ የተወለድኩ ነኝ። በማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል የሚደርሰው ግፍ እና እልቂት ያመኛል። በዛው ልክ የትግራይ ህዝብ እራሱን በአምላኩ ሳይሆን በህውሃት ጥበቃ እየኖረ እንደሆነ እንዲያስብ ብዙ የተሰራ ይመስለኛል። በእምነቱም ለዘብተኛ እንዲሆን ከ20 አመታት በላይ ሲሰራ ቆይቷል እንዲ እንድል ምክኒያት የሆነኝ በአጋጣሚ ያገኘዋቸው መነኩሴ ነን ባዮች የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች የእምነት እና የስነምግባር ችግር ነው። እኔ በበኩሌ ተስፋ ወደመቁረጡ እየሄድኩ ነው።

Anonymous said...

በጣም ትልቅ መልዕክት ነው፡ በቅዱሳን አባቶች ተጋድሎ እዚህ የደረሰቺው ኦርቶዶክስአዊት ኃይማኖት እና ይህች ቅድስት አገር ኢትዮጵያ ሁሉም ምዕመን በአንድ ላይ ኃይማኖቱንና አገሩን ሊጠብቅ ይገባል፡፡

Anonymous said...

God bless you all who initiated this whole idea.Pray to God for this idea not poisoned by those few who are intoxicated by the wealth and power stolen from Ethiopian people to continue their devide and conquer rule.Now time is coming to end up this.The dictator's day is on the way of downing. People from Tigray who are real sons of Ethiopia should speak out loudly by isolating themselves from the crowd of few anti Ethiopian sons of "Banda". In simple terms traitors.
We also pray to God to give us a heart of mercy and to initiate intellectuals who have good vision for Ethiopian most of them are under custody and in exile to put the way forward how the future Ethiopia to be under the rule of low.Let the spirit of God be upon us to give us unity.

Anonymous said...

ወንሜ ጽሁፉን በትእግስት አነበብኩት አጠቃላይ መልእክቱ ግን ከአማራ በሰተቀር ለዚች አገር የሚያስብ እና የሚመራ ከመጣ ትጠፋለች ነው

Anonymous said...

ወንሜ ጽሁፉን በትእግስት አነበብኩት አጠቃላይ መልእክቱ ግን ከአማራ በሰተቀር ለዚች አገር የሚያስብ እና የሚመራ ከመጣ ትጠፋለች ነው

Anonymous said...

በጣም ወቅቱን የጠበቀ መልእክት ነው እኔ ራሴ ትግሬ በመሆኔ ብቻ ራሱን የቻለ ፍርሃት አድሮብኛል ይህን ጽሑፍ ራሱን ወደ ትግርኛ ተተርጉሞ ብናቀርብ የበለጠ ትምህርት ሰጪ ነው ።ኤፍሬም ግን በጡመራ መድረክህ ላይ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ ብለህ መጥፈትህ ሁሌ ያናድደኛል ብዙ አንባቢያን ጡመራህን እንወዳለን እባክህ ይታሰብበት ።(እስኩ ድግሙ ነኝ ከጀርመን)

Anonymous said...

Stop your poisoning idea

Anonymous said...

ወንድሜ ኤፍሬም ጽሁፉ ከረፈደ የመጣ ነው ፤ጊዜውን የጠበቀ አይመስለኝም።ዘረኝነት ሐገሪቷንም ሆነ ቤተክርስቲያንን ካጥለቀለቀ ከ25 አመት በላይ ሆኗል።ቢሆንም አሁን ትንሽ ጭላጭ ተስፋ ያለው በትግራይ ህዝብ ነው ።የትግራይ ሕዝብ አታጣሉኝ ብሎ ከመንግስት ሕውሐት ጋር ካልተጣላ ወደፈራነው ነገር እየሄድን ነው። መቸም እንኳን ሰው እንስሳ እንኳን ዱላ ከበዛበት መልሶ ማጥቃቱ የማይቀር ነው።እኛም መሮናል ።ከትንሽ ጊዜ በሗላ የዋሁ ምንም ጥቅም ያላገኘው ትግሬ ሁሉ እንደጠላት ተቆጥሮ የጥቃት ሰለባ መሆኑ የማይቀር ነው።የገዛ ወንድሞቻችን መሆናቸውን እያስረሳን የመጣውን ጠላት አብረን እንታገል።

Anonymous said...

የገዛ ወንድሞቻችን መሆናቸውን እያስረሳን የመጣውን ጠላት አብረን እንታገል።

Blog Archive