Saturday, August 13, 2016

ቅሬታና አመጽ፡- የለውጥ መጀመሪያ (ማዕበል የአብዮት ዋዜማ)

አዲስ አበባ ለብዙ ዓመት የኖርኩት አዋሬ ነበር። ጠዋት ወደ ሥራዬ ሳቀና፣ ባለወልድንና ሥላሴን በቀኝ፤ እነ በዓታን፣ ኪዳነ ምህረትንና ግቢ ገብርኤልን በግራ አልፌ ነው የምሔደው። በርግጥ ፓርላማውንና ቤተ መንግሥቱን እንዲሁም አሸዋ ቆልለው ምሽግ ቢጤ የሠሩ፤ በምን አመካኝተን ሰው እንደብድብ የሚሉ የሕወሐት ወታደሮችንም አልፌ ነበር የምሔደው። እናም የአብያተ ክርስቲያናቱ በዓላት በሚሆኑበት ጊዜ ግራና ቀኝ የሚቀመጡት የኔ ቢጤዎች የሚለምኑበት ዜማ አንዳንዴ አፌ ላይ ተለጥፎ ይቀራል። በተለይ አንዳንዶቹ የኔቢጤዎች እጅግ የሚያምር ድምጻቸው ከሰው ጆሮ ቶሎ አይጠፋም። አንዳንድ ቃላትም ሳትፈልጓቸው ተደጋግመው ሲነገሩ ትሰሙና ጭንቅላታችሁ ውስጥ ተቀርቅረው ይቀራሉ። ልክ እንደየኔ ቢጤ የልመና ዜማ፤ ጠዋት ሰምታችሁት ቀኑን ሙሉ በልባችሁ ስታንጎርጉሩት እንደምትውሉት። ከነዚህ ቃላት መካከል የሕወሐት ሰዎች የሕዝቡን ተቃውሞ ለማጣጣል በፈረንጅ አፍ ቃለ ምልልስ በሰጡ ቁጥር የሚያነሷት «Grievance/ግሪቫንስ» የምትል ቃል ጆሮዬን ስትጠልዘው ከርማ ከውስጤ አልወጣ ብላለችና ጽፌ ብገላገላትስ።

በርግጥ Grievance/ግሪቫንስ ቅሬታ ማለት ነው። ቅሬታ የተለያየ ደረጃ ሊኖረው ይችላል። ጌታቸው ረዳ ሕዝቡ ያለው «ቀላል ቅሬታ» እንደሆነ ደጋግሞ ሲናገር ሰምቼዋለኹ። ሌሎች የክልል ባለሥልጣናትም «ችግራችን የመልካም አስተዳደር እጦት ነው» ይሉና ነገሩን በቀላል ቅሬታ ተርታ ለማስቀመጥ ይዳክራሉ።
ቅሬታ የየትኛም የሥራ አካል አንዱ መገለጫ በመሆኑ በተለይም በሰለጠነው ዓለም ሰዎች ቅሬታቸውን የሚያቀርቡትና መፍትሔ የሚያገኙበት ግልጽ መመሪያ ያዘጋጃሉ። አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም ቦታ ቅሬታ የሚያስተናግድበት መንገድ ሊኖረው ይገባል። ይህም የሕዝብን/ የተጠቃሚን መብት የማወቅና አገልግሎት ሰጪው ደግሞ ራሱን ተጠያቂ የሚያደርግበት አንዱ መስመር ነው።
ቅሬታ አቅራቢዎች የተለያዩ አካላት ሊሆኑ ይችላሉ። የድርጅቱ ሠራተኞች ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ድርጅቱ አገልግሎት የሚሰጣቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የስልክ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትም ሆነ ለሕክምና የተቋቋመ፤ ተማሪዎችን አስተምሮ ለቁምነገር ለማብቃት የተመሠረተ የትምህርት ተቋምም ሆነ ስልክና ኢንተርኔት በየቤቱ የሚያደርስ የቴክኖሎጂ ድርጅት በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ቅሬታ ላለው አካል ግልጽ ሆነ የቅሬታ ማቅረቢያ መንገድ መዘርጋት የቢዝነሱ አንዱና ዋነኛው ክፍል ነው።
አንዳንድ ድርጅቶች አገልግሎት መስጠት እንጂ ቅሬታ መቀበል ላይ ዝንጉዎች በሚሆኑበት ወቅት ይህንን የሚከታተሉና የተጠቃሚውን መብት የሚያስከብሩ የተለያዩ ድርጅቶች ይኖራሉ። ይህንን አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ዌብሳይቶችም እጅግ ብዙ ናቸው። አገልግሎት ተጠቃሚው አዲስ ኮንትራት ውስጥ ከመግባቱ በፊት አገልግሎት ሰጪው ድርጅት ምን ዓይነት ስምና ዝና እንዳለው ለማጣራት መሞከር የተለመደ ነው። ብዙ ቅሬታ የሚቀርብበት ድርጅት ውስጥ ለመግባት ማንም አይፈልግም። ስለዚህም ወደሌሎች ይሄዳል። እናም ድርጅቶች ለስማቸው መጠንቀቅ የቢዝነሳቸውና የሕልውናቸው አካል የሚሆነው የሞትና ሽረት ጉዳይ ስለሆነባቸው ነው።
መንግሥትም በሕዝብ የተመረጠና የተሾመ ሲሆን የሕዝቡን ቅሬታ መከታተል እጅግ ወሳኝ ይሆንበታል። ሕዝብ ከመንግሥት የሚያገኘው ነገር ካላስደሰተው በሚቀጥለው ምርጫ ዋጋውን ይሰጠዋል። ስለዚህም ፖለቲካን እንጀራ ያደረጉ ሰዎች ለሰው ቁብ የሌላቸውም እንኳን ቢሆኑ ለስማቸው መጨነቃቸው ግዴታቸው ነው። በምርጫ እንደተሾመ በምርጫ ወንበሩን ያጣልና። እንደ ኢትዮጵያ ያለ በሕዝብ ያልተመረጠ እና የሕዝብ ቅሬታ ምንም ለውጥ እንደማያመጣበት የሚያስብ ድርጅት ግን ሕዝብ ቅሬታ እንዳለው በአማርኛም በእንግሊዝኛም እየተናገረ ነገር ግን ለውጥ ለማምጣት ምንም ነገር አያደርግም። ጭራሹኑ ቅሬታ የሚያነሱትን አካላት እንደ ሰይጣን፤ ቅሬታ ማንሳታቸውን እንደ ትልቅ ኃጢአት በመቁጠር መግለጫ ይሰጣል፣ ገዳይ ፖሊሶቹንም ያሰማራል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ «ቅሬታ» ምንድነው? «መብራት ጠፋብኝ» ነው? አይደለም። «ውኃና ሌሎች አገልግሎት አላገኘንም» ነው? አይደለም። በሌሎች አገሮች ደም የሚያፋስሰው «የነዳጅ እጥረት» ነው? አይደለም። «የኑሮ ውድነት እና የምግብና የሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በሺህ ፐርሰንት አደገ እና መኖር አልቻልንም» ነው? አይደለም። (እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በሌላ አገር ቢሆን ኖሮ ያንን መንግሥት ከመሠረቱ ነቅለው የሚጥሉ ጉዳዮች ነበሩ።) ታዲያ የሕዝቡ ጥያቄ ምንድነው? «ሕልውናችን ጥያቄ ውስጥ ገብቶብናል፤ማንነታችንን የሚሰርዝ የሚደልዝ ከባድ ችግር ገጥሞናል፤ ሌላውን ሁሉ ችግር «ያልፋል» እያልን ችለን ነበር። ነገር ግን ሕለውናችንን የሚያጠፋውን ነገር ግን ልንታገሰው አንችልም» የሚል ነው። ይህንን ጥያቄ ነው እንግዲህ ጌታቸውን ረዳ እና አንድ የዘመኑ ልጅ (ስለ ኑሮ ምንነት ወይ በመኖር ወይ በትምህርት ያልተረዳ፤ በዕውቀቱም በዕድሜውም ያልበሰለ) በአልጀዚራ ለማብራራት ሲሞክሩ የሰማኹት።  
የፖለቲካ ምሁራን እንደሚናገሩት ቅሬታ ያለበት ሕዝብ ሁሉ ቅሬታውን ለመግለጽ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት አደባባይ ሲወጣ የሚገጥመውን ነገር ያሰላል። ትርፉንና ኪሳራውን ይገምታል። አደባባይ ለተቃውሞ ያልወጣ ሕዝቡ በሙሉ ቅሬታ የሌለበት ስለሆነ አይደለም። የሚጠብቀውን ስለሚያውቅ ጭምር ነው። በሌሎች ዲሞክራሲ በተለመደባቸው አገሮች የሕዝብ አደባባይ መውጣት ከሰው ሕይወት መጥፋት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ስለሌው ጦር ሜዳ እንደሚሄድ ሰው ለተቃውሞ የሚወጣ ሰው ቤተሰቡን ተሰናብቶ መሔድ አይጠበቅበትም። እንደ ሕወሐቷ ኢትዮጵያ ያሉት ግን ሕዝባቸውን አደባባይ ማየት ማለት የንቀት ምልክት አድርገው ስለሚቆጥሩት ለተቃውሞው የማይመጥን ርምጃ መውሰድ ይወዳሉ። ቀጥለው «የተወሰደው ርምጃ ተመጣጣኝ ነው አይደለም» ብለው ይቀልዳሉ።
ስለዚህ ሕዝብ ቅሬታ ስላለው ብቻ ሳይሆን የሚወጣው የቅሬታው ደረጃ ከፍ ሲል መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልገናል። አነስተኛ መካከለኛና ከፍተኛ ቅሬታ ብለን ብንከፍለው፣ በኢትዮጵያ ዓይነት አገሮች ሕዝብን ለአደባባይ ተቃውሞ የሚጋብዘው ከፍተኛው መሆኑን ልብ ይሏል። ከፍተኛ ቅሬታ ላይ የደረሰ አገር የሚያነሳው ተቃውሞ ከፍ ያለ እንደመሆኑ መንግሥትም የሚወስደው አፀፋ ከፍ ያለ ይሆናል። ይሁን እንጂ በአነስተኛ እና መካከለኛ ቅሬታዎች ጊዜ እንደነበረው ሕዝቡ የሚደርስበትን የአጸፋ ርምጃ ተሰቅቆ ተቃውሞውን ከማቆም ይልቅ የበለጠ እያሰፋው ይሄዳል። ይህም የዚያን ሥርዓት-አልባ መንግሥት መሠረቶች በመናድ ለውድቀት ያደርሰዋል።
አሁን በአገራችን የሚታየው የቅሬታ ደረጃ፣ የሕዝቡ ተቃውሞ እና የመንግሥት ምላሽ ይህንን የሦስተኛውን ደረጃ ይመስላል። በጥቃቅን ለውጦች ሊጠገን የሚችል ወይም ከባድ የአፈና ተግባር በመፈጸም የሚቆም ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥን በማምጣት ብቻ የሚጠናቀቅ ነው። በርግጥ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ጦር፣ እስከ ባለትዳር አልጋ የተዘረጋ የስለላ መዋቅር ቢኖርም ሥርነቀል ለውጥን ሊገታ አይችልም። ጦሩም ወደ ሕዝብ መተኮስ የሚያቆምበት፣ ስለላውም የሚፈረካከስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ይህ ደግሞ በታሪክ በብዙ አጋጣሚዎች የታየ እንጂ ለኢትዮጵያ ብቻ የሚነገር ጉዳይ አይደለም። ይህንን ለመረዳት ደግሞ ዕድሜ ከጠገቡት የሕወሐት ሰዎች በላይ ማንም ሊመጣ አይችልም። «ፋታ ፋታ ፋታ ያለው የእንዳልካቸው ካቢኔ» እንዴት እንደፈረሰ፤ ድርድር ድርድር ድርድር ያለው ወታደራዊ መንግሥት እንዴት እንደወደቀ ገና የትናንት ትዝታ ነው።
ለማጠቃለል፡- «ሕዝቡ ቅሬታ አለበት» በሚል እንደቀላል ጉዳይ ለመግለጽ የሚሞከረው ሐሳብ እንዴት ከባድና ጥልቅ እንደሆነ ተናጋሪዎቹም የገባቸው አይመስሉም። ቅሬታው ይዞት የመጣው ሕዝባዊ ቁጣ እና ማዕበል በቃለምልልስ ብዛት ወይም የድርጅታቸው አባላት በሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ማባበል የሚቆም እንዳልሆነ የሚረዱት ነገሩ ሲያልቅ ብቻ ነው። ብርሃኑ ዘሪሁን እንዳለው «ማዕበል የአብዮት ዋዜማ» ላይ ነን።         

No comments:

Blog Archive