Wednesday, August 17, 2016

ወርቅ አገር እና ኮረት አገር

አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ኮንሰርንድ (concerned) ሆኛለኹ ብላ ብዙ ጊዜ ስትናገር ሰምተናታል። አሜሪካ ግን እንዲህ በቀላሉ ኮንሰርንድ አትሆንም። በዓለም ላይ የሚነገረውን የሚፈ**ውን ሳይቀር የምታውቅ ከባድ አገር ስለሆነች፣ ከአይሲስ እስከ አልቃኢዳ አሸባሪዎች የሚያደርሱትን አያሌ ዘግናኝ ድርጊት በየደቂቃው ሲመዘግብ የሚኖር ቢሮክራሲ ባለቤት ስለሆነች በቀላሉ ኮንሰርንድ አትሆንም (አይኮነስራትም?)። ደግሞም በመካከለኛው ምሥራቅ ሲኒ ሲሰበር እንኳን ኮንሰርንድ እንደምትሆነው በሌላው ዓለም ተራራ የሚያክል ሕንጻ ቢደረመስ ላይኮነስራት ይችላል።

ለአሜሪካ ሁሉም አገር እና ሁሉም ሕዝብ እኩል ዋጋ አይሰጠውም፤ እኩል ሚዛን የለውም። ግብጽም አልጄሪያም ሁለቱም የሰሜን አፍሪካ አረቦች ቢሆኑም በአሜሪካ ሚዛን ግን ግብጽ ወርቅ ቢሆን አልጄሪያ ግን ተራ አሸዋ ነው። ሳዑዲና የመን ሁለቱም ጎረቤት አረቦች ቢሆኑም ሳዑዲ እንደ አልማዝ የመን ደግሞ እንደ ኮረት ነው የሚታዩት። ቻይናና ሞንጎሊያ ሁለቱም የእስያ አገሮች ናቸው። በአሜሪካና በምዕራባውያን ሚዛን ግን አንዱ አልማዝ አንዱ ኮረት ናቸው። ፓኪስታንና ባንግላዴሽ ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው። ለአሜሪካና ለምዕራባውያን ግን ፓኪስታን ወርቅ ቢሆን ባንግላዴሽ ገና ኮረት ነው።
ስለዚህም በግብጽ እና በሳዑዲ፣ በፓኪስታንና በሕንድ ጉዳይ በቀላሉ ኮንሰርንድ የምትሆነው አሜሪካ በአልጄሪያ እና በየመን፣ በባንግላዴሽና በማሌዢያ ጉዳይ ግን ብዙ መንገድ ካላለፈ በቀላል አይኮነስራትም። አሜሪካ ለምን አንዱን ወርቅ አንዱን ኮረት አድርጋ ትመለከታለች ሲባል ሌላ ምንም ትርጉም የለውም። ጥቅም ነው። የሚጠቅሟት አገሮች  ጉዳይ ያሳስባታል። መጡም ቀሩም ለውጥ ለሌላቸው አገሮችና ሕዝቦች ደግሞ ደንታ ሊኖራት አይችልም። ይህ «ለራስ አገር ጥቅም ቅድሚያ መስጠት» ሊያስኮንናት አይገባ ይሆናል፤ ፖለቲካ ስለሆነ። የዓለም ፖለቲካ ሁሉ ማጠንጠኛው ይኸው በመሆኑ አሜሪካ ብቻ የምትኮነንበት ነገር አይደለም።
ኢትዮጵያስ ለአሜሪካ ምንድናት? ወርቅ ወይስ ኮረት? ወርቅ ከሆነች በርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸመው እንቅስቃሴ ሁነኛ በሆነ መልኩ ይኮነስራታል። ኮረት ከሆነች ግን ለዲፕሎማሲው ያህል «ኮንሰርንድ» ሆኛለኹ ትበል እንጂ አንድምታው «እንደፍጥርጥራችሁ» የሚል ነው። ኢትዮጵያ ለአሜሪካ እና በጠቅላላውም ለምዕራቡ ዓለም ያላት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? በኢትዮጵያ የሚፈጠር ችግር በቀረው ዓለም «ስቶክ ትሬድ ገበያ» ላይ ምን ችግር ይፈጥራል። የሳዑዲ ንጉሥ ጉንፋን ሲይዘው የነዳጅ ዋጋ እንደሚንቀጠቀጠው እኛ ምን ብንሆን ነው በሌላው ዓለም ኑሮ ላይ ተጽዕኖ የሚኖረን? በሌላው ዓለም ላይ ያለን ተጽዕኖ እና ተፈላጊነት ሚዛን ባልደፋበት ሁኔታ ሌላው ዓለም በእኛ ጉዳይ ተጨንቆ እጁን ወደ እሳት ልኮ እንዲታደገን እንዴት ልንጠብቅ እንችላለን?

ከጥቂት ዘመን በፊት ሕንድና ቻይና፣ ብራዚልና ደቡብ ኮሪያ ለምዕራቡ ንግድ ከምንም የማይቆጠሩ ኮረቶች ነበሩ። አሁን ግን በዓለም የንግድ ከባድ ሚዛን ውስጥ የሚቀመጡ፣ ቢናገሩ የሚደመጡ አገሮች ሆነዋል። ኮረቶች የነበሩ ወርቅ ጆነዋል ማለት ነው በአጭሩ። አገራችን ለእኛ ወርቅ ብትሆንም ለእነርሱ ግን ወርቅነቷ አሁን አይታያቸውም። ስለዚህ በዚህ ዘመን ለኢትዮጵያ ከፈጣሪ በታች ያላት ተስፋ ሕዝቧ ብቻ ነው። «እኛ ሩዋንዳ አይደለንም፣ እኛ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አይደለንም እንደ ሕንድ እንደ ቻይና ትልቅ ታሪክ ያለን ትልቅ አገር ነን እንዲህማ በቀላሉ አንፈርስም፣ እርስበርሳችንም አንጫረስም» ብለን በተስፋ ለአገራችን ተስፋ መሆን ነው ይቺን ሐሳብ ያሬድ ጥበቡ ሲናገራት ሰምቼ እጅግ ደስ ብሎኛል)። ችግሩ የሚፈጠረው ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችን በአገራችን ጉዳይ እንደ ፈረንጆቹ «ኮንሰርንድ» ከመሆን ያለፈ ነገር የማድረግ ፍላጎት ካጣን ነው። ኮንሰርንድ ከመሆን የዘለለ ተግባር ይጠበቃል። 

1 comment:

Anonymous said...

"አገራችን ለእኛ ወርቅ ብትሆንም ለእነርሱ ግን ወርቅነቷ አሁን አይታያቸውም። ስለዚህ በዚህ ዘመን ለኢትዮጵያ ከፈጣሪ በታች ያላት ተስፋ ሕዝቧ ብቻ ነው። «እኛ ሩዋንዳ አይደለንም፣ እኛ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አይደለንም እንደ ሕንድ እንደ ቻይና ትልቅ ታሪክ ያለን ትልቅ አገር ነን። እንዲህማ በቀላሉ አንፈርስም፣ እርስበርሳችንም አንጫረስም» ብለን በተስፋ ለአገራችን ተስፋ መሆን ነው (ይቺን ሐሳብ ያሬድ ጥበቡ ሲናገራት ሰምቼ እጅግ ደስ ብሎኛል)።"

በእርግጥም ሃገራችን ውብ ናት ከእንቁም በላይ እግዚአብሔር ይጠብቅልን እርስ በርስ ከመጠፋፋት ይጠብቀን አሜን በርትተን እንጸልይ

Blog Archive