Wednesday, August 31, 2016

ቀልድና ሥላቅ፤ ብሶት መግለጫና ሰላማዊ መታገያ ዘዴ?

ሰው መሰሏ ፍጡር (ዝንጀሮ/ ጦጣ መሰሏ ፍጡር) ድንቅነሽ (ሉሲ) የሞተችው ከዛፍ ላይ ወድቃ መሆኑን «የዘርፉ ባለሙያዎች» (በትክክልም የዘርፉ ባለሙያዎች የሚለው ቃል የሚገባቸው ሰዎች) ግኝታቸውን ካሳወቁ ወዲህ ዜናው ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል። እኔ ከሰማኋቸው ውስጥ ቢቢሲ እና ኤን.ፒ.አር የተባለው ተወዳጅ የአሜሪካ ራዲዮ ደጋግመው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እንደ አቅሚቲ ደግሞ ኢቲቪም ዜናውን ማወጁን ከዚሁ ከፌስቡክ ተረድቻለኹ።
ብዙ ወገኖች አጋጣሚውን በመጠቀም ጥርስ የማያስከድኑ ቀልዶችን በኢቲቪ እና በኢሕአዴግ ላይ ሲያወርዱ ነበር። ብዙው ሰው ቀልዱን አገሪቱ ካለችበት አስጨናቂ ሁኔታ ትንሽ እረፍት መውሰጃ እንዳደረገው ያስታውቃል፤ እኔን ጨምሮ። አንድ ሁለት ወዳጆቼ ገና ለገና ኢቲቪን ለመውቀስ ይህንን ሳይንሳዊ ውጤት ማጣጣል ተገቢ እንዳልሆነ ሐሳባቸውን ኮምጨጭ ብለው አካፍለዋል። በርግጥ በቀልድ የተናገሩትም ሰዎች ይህ የሚጠፋቸው አይመስለኝም። አንድ ቁምነገር ግን በዚሁ አጋጣሚ ማስታወስ ፈለግኹ።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጨቋኝ መንግሥታት ባሉባቸው አገሮች፣ ጨቋኞች ላይ መቀለድ፣ ተግባራቸውን በሥላቅ ማንኳሰስ «ከሰላማዊ መታገያ መንገዶች» (nonviolent civil resistance) መካከል እንደ አንዱ መንገድ መታየት ያለበት ይመስለኛል። ይህ የጨቋኞችን «ማኅበራዊ ዋጋ መና የሚያደርግ» የሥላቅ ዘመቻ ጉልበተኞችንና ከእነርሱ ጋር በዝምድናም ይሁን በሥልጣን የሚወዳጇቸውን ሰዎች የሚፈታተንና የሚያሸማቅቅ ተግባር ነው። በጥንቱ ዘመን ባለሥልጣን «እረኛ ምን አለ?» ሲል በእረኛ ዘፈንም ይሁን ውኃ በምትቀዳ ሴት እንጉርጉሮ ወይም በአስለቃሿ የኃዘን ዜማ ውስጥ የሚጠቀሰውን ቆዳ ስር ገብቶ የሚቆነጥጥ ስላቅ ለማወቅ፤ በዚያም ጉድለትን እና የሕዝብን ብሶት ለመረዳት የሚደረግ ጥረት መሆኑን ማስታወስ ያስፈልገናል።
እንዲህ ያለው ስላቅ ከሰውም አልፎ አምላክን የሚሸነቁጥበት ጊዜ አለ። በአጥቢያው ያለች የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን በመቃጠሏ ያዘነ አንድ ምእመን፡-
«ከዚያ ከላይ ሆነህ ስታላግጥ በሰው፤
እናትህ ነደደች ሐዘንን ቅመሰው።» አለ አሉ።
የተከፋ ሰው አምላኩን በስላቅ ለመሸንቆጥ ወደኋላ ካላለ፣ በእሳት አለንጋ የሚገርፉትን ምድራውያን «አምላኮች» የማይሸነቁጥበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
የኢትዮጵያን የቀልድና የስላቅ ዓይነቶች በደምሳሳው እንኳን ብንመለከታቸው፣ ሕወሐት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ የሚቀርቡት ቀልዶች ፓርቲውን፣ የሚያሰማራቸውን ወታደሮች እና ባለሥልጣኖቹን የተመለከተ መሆኑን እንገነዘባለን። ከማስታውሳቸው መካከል ለምሳሌ፡- የተጨቆኑ ቀልዶች፤ የክበበው ገዳ የተለያዩ ቀልዶች፤ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚቀርቡ የተለያዩ ቀልዶችን መጥቀስ ይቻላል። በትግርኛ ቅላጼ የሚናገሩው ወታደሮች ላለፉት 25 ዓመታት የብዙ ቀልዶች ምንጭ ነበሩ። ጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት ጋር ሲደርሱ «ዋይ፣ አንዱ ደርግ ይኸውና» ከሚለው የ1980ዎቹ የመጀመሪያ ሰሞን ቀልድ ጀምሮ ብዙ ብዙ ተነግሯል። ገና ሥልጣን ከመያዛቸው አስቀድሞ ታማኝ በየነ የተናገራት ታዋቂ ቀልዱ መቸም አትዘነጋም። ወያኔ በሬዲዮዋ ይኼን ያህል ገደልኩ የምትለውን እየደመረ ይቆይና አሐዙን በዚያን ጊዜ ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ አድርጎት ሲያበቃ፣ «እና በዱቤ እየሞትን ነው ማለት ነው?» ሲል ይሳለቅባቸዋል። ቀልዶቹ በጅምላ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያልተሰነዘረ ነገር ግን አገዛዙን ለመንቀፍ የተወረወረ መሆኑን የምንገነዘበው የቀልዱንና የሥላቁን ይዘት ስንመረምር ብቻ ነው። 
ከአገዛዙ ወገን የሚቀለድበትን ቀልድ አሸንፎ የወጣው መለስ ብቻ ይመስለኛል። አማርኛ ያውም የስላቅ አማርኛ በደንብ የሚያውቅ መሆኑ ጠቅሞታል። በፓርላማ እና በሌሎች ስብሰባዎች የሚናገራቸው ቀልዶች፤ በተለይም ብቸኛው የሕወሐት አምባገነን ከሆነባቸው የ1990ዎቹ የሕወሐት ክፍፍል በኋላ  ራሱን ኤዲት ሳያደርግ እንደ ተራ ሰው የሚናገራቸው ነገሮች ቀልድ የሚፈጥሩ ሰዎችንም ሳይቀር ያሸማቀቀ ይመስለኛል። የማታ ማታ «አበበ ነኝ» ብሎ ለቪኦኤ ከመደወሉ በስተቀር ብዙ ነገር ማለፍ ችሎ ነበር። «አበበ ነኝ» ብሎ፣ ኋላም አበበ ገላው በአደባባይ ተቃውሞት ብዙም ሳይቆይ በመሞቱ ግን የማይፋቅ ስላቅ ፈጥሮ አልፏል።

እንግዲህ በዚህ ዘመን ስላቅ የትግል ዘዴ ሆኗል ብንል የሚያስኬደን ደግሞ የአበበ ቶላ (አቤ ቶክቻውን) «ዋዛና ቁምነገር» እና «ፉገራኒውስ»ን ስንመለከት ነው። በርግጥም ነገሩ ከጊዜያዊ ሳቅ የዘለለ የተቃውሞ መስመር ሆኗል ማለት ነው። ከዚህ አንጻር ስንመለከተው የሉሲን «ዜና-እረፍት» ተከትሎ መቀለድ በጭራሽ ሊታለፍ የማይቻል አጋጣሚ ይሆናል ማለት ነው። አንዱ ጎበዝ የማኅበረሰብ ጥናት ተማሪ ደግሞ «ቀልድ እና ፖለቲካ በዘመነ ኢሕአዴግ» የሚል የምረቃ ወረቀት ጽፎ ያስኮመኩመን ይሆናል። እስከዚያው ……. በዚቹ እናዝግም።   

1 comment:

Anonymous said...

"ይህ የጨቋኞችን «ማኅበራዊ ዋጋ መና የሚያደርግ» የሥላቅ ዘመቻ ጉልበተኞችንና ከእነርሱ ጋር በዝምድናም ይሁን በሥልጣን የሚወዳጇቸውን ሰዎች የሚፈታተንና የሚያሸማቅቅ ተግባር ነው።"
Dear brother Ephrem, I am disgusted with your labeling 'ከእነርሱ ጋር በዝምድናም ይሁን በሥልጣን የሚወዳጇቸውን ሰዎች'. For you, yezimdina relation is enough to categorize others as enemies. I can hear you loud and clear. Please don't pretend to be religious any more. Have you ever read about hate speech? The hate speech which you hail as a sign of civil resistance, is a secular crime. A person of your caliber (in terms of religious understanding) should have transcended the law. But your words prove that you applaud that kind of action. I understand many of us do similar mistakes during emotive times like this one, but I expect an apology thereafter.

One of your former students (in Christ).

Blog Archive