Monday, August 8, 2016

ማኅበራዊ ሰንሰለቱ (social fabric) ቀጥኗል ወይስ ተበጥሷል?

አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬባወጣው መግለጫ እንዲህ ብሏል። «The U.S. Embassy expresses its deep condolences to those who suffered as a result of the violence and regrets the damage to livelihoods, economic development, and the social fabric that such violence brings. ከሰሞኑ በተነሣው አለመረጋጋት በሰው ልጆች ሕይወት ላይ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እና በማኅበራዊው ግንኙነቱ ላይ ለደረሰው ጉዳት የአሜሪካ ኤምባሲ ጥልቅ ሐዘኑን ይገልጻል» ይላል። 
ኤምባሲው በመግለጫው የተጠቀማት አንዲት ኃይለ ቃል ላይ መወያየት አስፈላጊ ይመስለኛል። መግለጫውን ያላያችሁ ሰዎች ብዙም አላመለጣችሁም። ሁልጊዜ የሚወጣ የመንግሥታት መግለጫ ላይ አንዳንድ ዐ.ነገሮችን፣ ቀኖችን መቀየር ብቻ ነው። «እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው» ዓይነት ነገር ናት። ያንንም ያንንም ላለማስቀየም፣ ምንም አላሉም ላለመባል የምትወረወር «እንደፍጥርጥራችሁ» የምትል መግለጫ። አንበሳንና ሚዳቋን እኩል «አንተም ተው አንተም ተው» የምትል ጉልበተኛውን እና ጉልበት የሌለውን በአንድ ሚዛን የምታስቀምጥ ግፈኛ መግለጫ። ግርማዊ ቀ/ኃሥላሴ ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ ክንዷን ባነሳችበት ወቅት እንዲህ ባለው የመንግሥታቱ ድርጅት/ሊግ መግለጫ ተከፍተው ያቀረቡት ትንቢታዊ መግለጫ ዛሬም ድረስ የሚታወስ ትንቢታዊ ንግግር ሆኖላቸዋል። ሕዝቤን ከጣሊያኖቹ ባትታደጉ ግን «እግዚአብሔርና ታሪክ ውሳኔያችሁን ያስታውሱታል “God and history will remember your judgment.” እንዳሉት ሆኗል።  

ወደተነሣንበት ሐሳብ ስንመለስ ከኤምባሲው መግለጫ ትኩረቴን የሳበችው ኃይለ ቃል ያልኳት «social fabric» የምትለው ናት። በቀላሉ ማኅበረሰባዊ ሰንሰለት/ ማኅበራዊ ገመድ/፣ ማኅበራዊው ግንኙነት ብንለው ያስኬድ ይመስለኛል። (የሶሢዮሎጂ ምሁራን ሊተቹበት ይችላሉ።) የአሜሪካኖቹ መግለጫ አገራችን የገባችበት ቀውስ ይህንን ግንኙነት ጎድቶታል ነው የሚለው። እንዲህ በቀላል ነገር አስቀምጠው ማለፋቸው በርግጥ እጅጉን የሚገርም ነው። እነርሱ ተጎድቷል ያሉትን በተብራራ ሆኔታ ቢነግሩን ጥሩ ነበር። እስከዚያው ግን … የራሳችንን እንወርውር።
አንድን ማኅበረሰብ አያይዞ በአንድ ላይ የሚያኖረው የተለያየ ነገር ነው። እንደ ቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት፣ እንደ ሮማ ኢምፓየር ብዙ ማኅበረሰቦች በኃይል አንድ ላይ እንዲኖሩ የሚገደዱበት ጊዜ አለ። አጋጣሚው ሲመጣ እና እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ ያዋደዳቸው ኃይል ሲዳከም አንድነቱ ይፈረካከሳል። ተፈረካሷልም። ሌሎች ማኅበረሰቦች ደግሞ አንዱ ከሌላው የሚያገኘው እጅግ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እስካለ ድረስ አብረው ይኖራሉ። የአውሮፓን ሕብረት ወይም እንግሊዝኛ/ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ካናዳን ማንሣት እንችላለን። ደግሞ እንደ እኛ አገር ያለው በኃይል ነው እንዳይባል ኃይል በሌለበትም ዘመን አብሮ የኖረውን፤ በኢኮኖሚ ጥቅም ብቻ ነው እንዳይባል ይህ ነው የሚባል ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት የማይታይበት ማኅበረሰብ ደግሞ ባለው ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር አብሮ ለዘመናት ኖሯል።
ማኅበራዊ ትስስሩን የፈጠረው ሃይማኖት ብቻ አይደለም። የተለያየ ሃይማኖት ስላለን። አንድ ብሔረሰብ መሆንም አይደለም። ከ80 የምንበልጥ ብሔረሰቦች ነን። መልክዐ ምድራዊ ተመሳሳይነትም አይደለም። ደጋው ወይና ደጋው ቆላው በሙሉ በኢትዮጵያ አለ። የቆዳ ሥፋታችን ትንሽ አገር ስለሆንም አይደለም። በአፍሪካ ካሉት አገራት ከትልልቆቹ ከሦስቱ መካከል ነን። የአገራችን የትስስሩ አስኳል ከላይ የተዘረዘረው ሁሉ ተደባልቆ፣ በዘመን ብዛት የፈጠረው ራሱን የቻለ ልዩ ንጥረ ነገር ነው ባይ ነኝ። ይህ ልዩ የአንድነት ገመድ በብዙ ችግር ሳይበጠስ በመቆየት ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን አስመስክሯል።
ይሁን እንጂ በስታሊናዊ የማኅበረሰብ አንድምታ የሚመራው ግራ ዘመም የአገራችን ምሁር ላለፉት 60 ዓመታት ባቀነቀነውና «ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ድምር» ብቻ እንጂ የአንድነቷ ምስጢር ከዚህ በላይ የሆነ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ በማበከር በሠራው ያላሰለሰ ሰበካ ይህ ማኅበራዊ ትስስር ከባድ አደጋ ሊገጥመው ችሏል። ትስስሩ ለአደጋ የተጋለጠው በተለይ መንበረ መንግሥቱን የተቆጣጠረው የግራ አክራሪው ሕወሐት ከብሔረሰቦች ውሕድነታችን ውጪ ያሉ ገመዶችን ሁሉ ለመበጣጠስ ያደረገው ሰፊ ሥራ ነው። ስለዚህም አገር ማለት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥርቅም እንጂ ሌላ ምንም ነገር አይደለም የሚለውን ሐሳብ የያዘው አደገኛ ቦንብ እነሆ በመፈንዳት ልይ ይገኛል።
ሕወሐቶች ኢትዮጵያን ለመረዳት ከመጣር ይልቅ እነርሱ የሚፈልጓትን «አዲሲቱን ኢትዮጵያን» ለመፍጠር ኢንቨስት ባደረጉት አገሪቱን የማይመጥን ሥራ ራሳቸውንም አገሪቱንም ለአደጋ አጋልጠዋል። በሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስር በጣጥሰዋል። ማንም ሰው ከራሱ ብሔረሰብ አጥር ወጥቶ መኖር እንዳይችል፣ ማሰብ እንዳይችል አድርገዋል። በሌላ ክልል የሚኖረውም በባዕድ አገር እንደሚኖር እንዲሰማው፣ ከቻለ ወደራሱ ክልል እንዲሄድ ካልቻለ ደግሞ ምንም ድምጽ ሳይኖረው በባይተዋርነት እንዲኖር አድርገዋል። ከብሔረሰቡ ውጪ ያሰበውንም እንደ ወንጀለኛ በመቁጠር የተለያየ ስያሜ በመለጠፍ ከጨዋታው ሜዳ አስወጥተውታል።
የሕዝቡን ትስስር ያጠበቁ እና በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያልነበሩ ተቋማት ለፖለቲካ ፍጆታ በሚል በመደፍጠጣቸው፣ የተረፉትም በፓርቲው ቁጥጥር ሥር በመዋላቸው፣ ሕዝብ ተመካክሮ ችግሩን ሊፈታባቸው የሚችልባቸውን ቁልፎቹን ሁሉ አጥቷል። ዘመን ያመጣው ማኅበራዊ የትስስር ገመድ ሊሆኑ የሚችሉትን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን (መያዶችን) እንኳን አዲስ ባወጣው «የመያዶች ሕግ» ቀርቅቦ በመያዙ፣ ገሚሶቹንም በማፍረሱ ዛሬ አገራችን በችግር ሰዓት ሊታደጋት የሚችለውን የአደጋ ጊዜ መውጫ በሙሉ እንድታጣ ሆናለች።
የምድራዊ መንግሥት እንደራሴ ያልሆኑት ሃይማኖቶች በፓርቲው ቁጥጥር ሥር ገብተዋል። የኦርቶዶክስን መንፈሳዊ የሥልጣን ተዋረድ (ከፓትርያርክ እስከ አቃቢት) በራሱ የፖለቲካ አስፈጻሚዎች ተቆጣጥሮታል። የእስልምና ተቋማትንም እንዲሁ። መዋቅራዊ ሰንሰለት የሌለባቸውን የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶችንም በየተናጠላቸው እንደሚያዝዝባቸው ይታወቃል። ይህ መጠን የለሽ ጣልቃ ገብነት የሕልውናው ማስተማመኛ የሆነ ቢመስለውም የቀኑ ቀን ግን ሊታደገው የሚችለውን የአደጋ ጊዜ መውጫ ድልድይ እንዳፈረሰ አልተገነዘበውም። ስለዚህም ይህንን ግራ አክራሪ ፓርቲ የሚቃወሙ በሙሉ እርሱ የሚያዝዝባቸውን የሃይማኖት ተቋማት ጭምር ለመቃወም ይገደዳሉ። ምክንያቱም በፖለቲካ ፓርቲውና በእነዚህ የቤተ እምነቶች አስተዳደር መካከል ያለው ልዩነት ስለጠፋ።
እነዚህ የሃይማኖት ቤቶች በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን ማብረድ፣ አደጋዎችን መቀልበስ የሚችሉበት ታላቅ ሰማያዊ ኃይል ተሰጥቷቸው ሳለ ፓለቲካው ይህን ጸጋ ቀምቷቸው ከማንኛውም ዓለማዊ ድርጅት የማይሻሉ ድኩማን አድርጓቸዋል። ስለዚህም ችግር ሲኖር ለሕዝባቸውና ለአማኛቸው ተገብተው ለመናገር ፍላጎት የላቸውም። ቢናገሩም የሚሰማቸው የለም። ልብሳቸው የሃይማኖት ከመሆኑ ውጪ አቋማቸው ግን እንደማንኛውም ዓለማዊ ድርጅት በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ከበሬታም ሞገስም የላቸውም።
ስለዚህ አገራችንን ደግመን መገንባት በምንችልበት ወቅት እነዚህን ማኅበራዊ ትስስሮች ለመጠገን፣ የቆሰሉትን ለማከም ካልቻልን የመንግሥት ለውጥ ብቻ ለአገራችን አንድነት ዋስትና አይሆንም። አገራችን እንደ ሩዋንዳ ወይም እንደድሮዋ ዩጎዝላቪያ እንዳትሆን ሲባል የማይመጣ መስሎን ለነበርን በሙሉ ነገሩ ሊሆን እንደሚችል ያሰጋን በዚህ ምክንያት ነው። «አይመጣምን ትተሽ፤ ይመጣልን ያዢ» እንዲል ተረታችን። ስለዚህ ማኅበራዊ ትስስራችንን ከመበጠስ እንዲተርፍ እንሥራ። ፖለቲካዊ ለውጥ ብቻ ለአገራችን የሰላም ዋስትና አይደለም።   

2 comments:

Ermias Tesfaye said...

Correction: we are not in one of the three largest countries in Africa , as far as land size but the tenth largest country .I think you confused it with population size.

Anonymous said...

አሜሪካኖቹ ወደ ማህበራዊ ገመዱ ያመለከቱበት ምክንያት እነሱ የዘሩትን እንክርዳድ እና የጉዳት ዘር ስለሚያውቁና ቡቃያውንም ስለሚጠብቁ ነው። የኢትዮጵያ መሠረቷ፣ እንዲሁም የተያያዘችበትና ለረጂም ጊዜ የኖረችበት የህልውና ገመዷ እግዚአብሔር ነው። ከብዙ የቅኝ መግዛትና የመድፈር ሙከራ ውድቀት በኋላ ይህን ቁልፍ እውነታ ፈረንጆቹ ተረዱት። ኢትዮጵያውያን ግን ዘነጉት። ይህን መሠረቷን ካላፈረሱ፣ የህልውናዋን ገመዷንም ካልበጠሱ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ኃብት ለመውረስ እንደማይችሉ ፈረንጆቹ ስለተረዱ ነው ዘመቻቸውን በኃይማኖቷ ላይ አነጣጥረው የጀመሩት። ዐረቦች እስልምናን በመጠቀም የሰዎችን አዕምሮ ተቆጣጥረው የአፍሪካን ሲሦ፣ መካከለኛውን ምስራቅና የተወሰኑ የእስያ መልክአ ምድሮችንና ሃብቶችን የራሳቸው አድርገዋል። ምዕራባውያን ፈረንጆችም ይህን ዐረቦች ያገኙትን ጥቅም ሲያዩ የፈለጉትን ነገር ለማግኘት የሰውን አዕምሮ መቆጣጠርን የመሰለ መሣሪያ እንደሌለ ተገነዘቡ።

ታዲያ ፈረንጆች የኢትዮጵያውያንን አዕምሮ ተቆጣጠሩ ወይ? እንዴትስ ተቆጣጠሩ? መልሱ አዎ ተቆጣጠሩ ነው። የተቆጣጠሩትም ኢትዮጵያውያንን ርዕዮተ ዓለም በማስታቀፍ ነው። አሁን ብዙ ኢትዮጵያውያንን በተለይም ዘመናዊ የምዕራባውያን ትምህርት የቀመሱትን የለከፈው የሊበራል ርዕዮተ ዓለምን ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት ፈረንጆች ናቸው። ዘመናዊ የምዕራባውያን ትምህርት በተለይ ለኢትዮጵያውያን የአዕምሮ ቅንነትን ወይም ለበጎ ሥራ ትጋትን ወይም በጥበብ ማስተዋልን አታጎለብትም። ነገር ግን ለኢትዮጵያዊው 'በራስህ አስተያየት ጠቢብ ትሆናለህ' እያለች በመደለል ቃልን ታለዝባለች፣ አዕምሮን ታጎድላለች። ኢትዮጵያዊው ለምዕራባውያን የሩቅ ዓላማ ተገዢ እንዲሆን፣ በነሱም እንዲዋረድ፣ ክብሩንም ለነሱ እንዲሰጥ፣ ድካሙንም እንዲወስዱ፣ በተፈጥሮ ሀብቱም እንዲጠግቡ ታጠምደዋለች። ዘመናዊ የምዕራባውያን ትምህርት ሊበራሊዝምን ያራምዳል። ማርክሲዝም ሌኒኒዘምን ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡትም ምዕራባውያን እንደሆኑ እራሳቸው ምዕራባውያን በፅሁፍ መስክረዋል። ኢህን ያደረጉትም የአፄ ኃይለስላሴን መንግሥት ለመጣል ነበር። የአፄ ኃይለስላሴ መንግሥት እንዲወድቅ የፈለጉትም "ዲሞክራሲ" በሚል የነሱ መፈክር ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ከምሰሶዋ ጀምሮ ለማፍረስ ነበር። ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ካፈረሱ የኢትዮጵያን መሠረት እንደሚያናጉና የህልውና ገመዷን እንደሚበጥሱ ያውቃሉ።

ፈረንጆች ርዕዮተ ዓለማቸውን በኢትዮጵያ ያሰራጩት በብዙ መንገድ ነው። በትምህርት ቤት፣ በዩኒቨርቲዎች፣ በመፃህፍት፣ በፊልሞች፣ የፕሮቴስታንት ኃይማኖትና አይነቶችን በማባዛትና በማሰራጨት፣ እነሱ ባስቀመጡት መንግሥት ፖሊሲዎች እና በሌሎችም መንገዶች ነው። እነ ዋለለኝ መኮንን የዚህ ወጥመድ ሰለባ ናቸው። እነ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ እነ መለስ ዜናዊ ሁሉ በዚች በአሳች ትምህርት ወጥመድ የተጠመዱ፣ በስለቷም የተወጉ ነበሩ። አሁንም ብዙዎቹ (ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ የተዋህዶ አማኞችን ጨምሮ) ወደ መንገዷ ያዘነበሉ ናቸው። ኢትዮጵያዊውያን አሳቿ ባስተማረቻቸው ልዝብነት በራሳቸው ጥበብ እንሄዳለን ብለው የእግዚአብሔርን ጉዳይ ጣል አድርገው እግዚአብሔርን ከጣዖት ጎን በሚያሰልፈው በጣዖተ 'ዲሞክራሲ' ጎዳና ጉዟችን እንቀጥላለን ካሉ፤ እነሆ ጥፋት እንደ አውሎ ነፋስ በድንገት መጥቷል። የመበታተን መከራን ማን ይቋቋማል? የኢትዮጵያዊው የመንቀሳቀሻ ክልሉ ከጠባብ እስር ቤት እያነሰ ሲመጣ፣ መረማመጃ እንደተወጋ ትንፋሽ ሲያጥር፣ ሰላም እንደ እናት ስትናፈቅ፣ አንድነት እንደ ውኃ ሲጠማ፣ ምዕራባውያን "ጎረቤት አገሮች ሆናችሁ ተስማምታችሁ እነድትኖሩ ልናግባባችሁ መጣን" እያሉ ሲሳለቁ፤ ያን ጊዜ ኢትዮጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ዲሞክራሲን ፍሬ ይበላሉ፣ በእጦትም ይጠግባሉ። የተናቀችው ምርጧን ቢጠሯት እነሱ ጥሪዋን አልሰሙምና በነዚህ በፌዘኞች ላይ ትስቃለች። ሰለዚህ የሚያዋጣው ሳይውሉ ሳያድሩ የምዕራባውያንን ድሪቶ ወደ ገደል በመጣል ወደ ቀደመው ወደ አባቶቻችን የማህበረሰብ፣ የባህልና የአሰተዳደር ሥርአት መመለስ እንጂ ልዝብ ሽንገላ አይደለም።

Blog Archive