Thursday, September 1, 2016

ከሚዲያዎች ትልቅ ጥበብንና ጥንቃቄን የምንፈልግበት ጊዜ ነው

በአጠቃላይ .......

ዘመኑ ሬዲዮና የቴሌሺዥን ከመሆን አልፏል። በሙያቸው ጋዜጠኝነት የተማሩ የተመራመሩ ሰዎች ብቻ በማንኪያ እየቆነጠሩ መረጃ የሚያቀብሉበት ዘመን አልፏል። ዘመኑ የማኅበራዊ ጋዜጠኝነት/ citizen journalism (ሁሉም እንዳቅሙ ዜና የሚዘግብበት) ዘመን ነው። ይህ ማለት ግን የሚዲያ ባለቤቶችና ባለሙያዎች አሁንም የመሪነቱን ሥፍራ እንደያዙ መሆናቸው ቀርቷል ማለት አይደለም። የተለያየ መረጃ ከሁሉም ቦታ የቃረመ ሰው እውነታውን ለማረጋገጥ ዞሮ ዞሮ ወደ መደበኛዎቹ ሚዲያዎች ብቅ ማለቱ የግድ ነው።
የኢትዮጵያውያን የመረጃ ግብይትም ከፍ ብለን የጠቀስነውን ነው የሚመስለው። አገራችን ባለችበት በዚህ ሁኔታ ዜጎች መረጃዎችን በገፍ ያቅርቡ እንጂ መረጃውን አበጥረውና አንጠርጥረው መልሰው በማቅረቡ በኩል አሁንም የሚዲያዎች ኃላፊነት እንደተጠበቀ ነው፡፡ ዘመኑ የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የዜናና የመረጃ ጦርነትም ዘመን ነው። በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች እየተፈፀሙ ያሉትን እጅግ ዘግናኝ ወንጀሎች ሕዝቡ በመዘገብ ሚዲያዎቹ ደግሞ አቀናብሮ መልሶ ለሕዝቡ በማድረስ ትልቅ ውለታ በመዋል ላይ ናቸው። ኢሳት፣ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ እና መንግሥታዊዎቹ የአሜሪካና የጀርመን ድምጾች እንዲሁም ዋዜማ የኢንተርኔት ሬዲዮ በመረጃ ግብዓትነት የምከታተላቸው ባለውለታዎቼ ናቸው። በድረ ገጽ በኩልም ሊጠቀሱ የሚገባቸው እጅግ ብዙ ባለውለታዎች አሉን።
በግለሰብ ደረጃም ከሚዲያዎች ባልተናነሰ የዜና እና የመረጃ ምንጭ መሆን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ የሐሳብ ግብይቱን (ዲስኮርሱን) ቅርጽ በመስጠት ትልቅ አገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ያሉ ወገኖቻችን አያሌ ናቸው። ለጊዜው ስማቸውን ከመዘርዘር ልቆጠብ። ደግሞስ ማንን አንስቼ ማንን ልተው ነው?
ሥጋቴ ......
-----

ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ ሁሉ የመረጃ ግብዓት እና የሐሳብ ስለቃ ሕወሐትን እጀ ሰባራ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ ጥንቃቄ ካልተደረገባቸው ሊጎዱን የሚችሉ ተያያዥ ችግሮች ይታዩኛል።
በመጀመሪያ መረጃዎቹ የመምጣት ፍጥነታቸው ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሣ (በተለይ ሚዲያዎቻችን) ሆን ተብለው የሚለቀቁ የሐሰት ዘገባዎችን በማሰራጨት ትግሉን እንዳይጎዱት እሰጋለኹ። ሆን ብሎ የሐሰት ዘገባን በማሰራጨት እና የዚያን ዘገባ ሐሰትነት «በማጋለጥ» ሌሎች ዘገባዎች ታማኝነት እንዲያጡ በማድረግ በኩል የሕወሐት ማሽን እንደሚሰራ መታወቅ አለበት።
በመቀጠልም ሚዲያዎቻችን ትክክለኛውን የትግሉን ደጋፊና አጋር አጋጣሚውን ለመጠቀም ከሚሞክሩት «ኦፖርቺንስቶች» ባለመለየት መድረካቸውን እንዳያበላሹትም እሰጋለሁ። ሕወሐት የአስተዳደር ችግር አለብኝ ብሏል። ያንን ላስተካክል ዕድል ስጡኝ እስከዚያው ልግደላችሁ እያለ ነው። ይኼንኑ ሐሳብ በሌላ አማርኛ በማቅረብ ሚዛናዊ ለመሆን ለሚጥሩ እና ትግሉን ለሚጎትቱ ሰዎች ዕድል መስጠት አይገባም። በመስመጥ ላይ ካለው የሕወሐት መርከብ ለመትረፍ የሚዘሉና በአጋጣሚ ከሕዝብ መርከብ ላይ የሚያርፉ በሙሉ ዋና ዓላማቸውን የዘነጉ ናቸው ብሎ በየዋህነት በመደምደም የማይገባ ድምዳሜ መስጠት ትግሉን ይጎዳል።
++ ከዚህ አንጻር ሚዲያዎቹ በሕቡዕ ከተራጁ ቡድኖች የሚመጡላቸውን እና ለማጣራት የሚያስቸግሩ መልእክቶችን «እንደወረደ» ከማቅረባቸው በፊት የነገሮችን አካሄድ የሚያረጋግጡበትን መንገድ ቢያመቻቹ፣ የተሣሣተ መረጃ ቢያቀርቡ እንኳን (በየትኛውም ትልልቅ ሚዲያ እንደተለመደው) ያለምንም ይሉኝታ ቶሎ ቢያስተባብሉ፤
++ ሆን ተብለው የሚሰራጩ የሐሰት ዘገባዎችን፣ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ሕዝቡ ራሱ እንዲያጣራቸው እና እውነተኛውን ከሐሰተኛው መለየት እንዲችል አቅጣጫ ቢጠቁሙ፣
++ ለምሳሌ ያህል በአገራችን ያልተነሱ ፎቶዎችን ከኢትዮጵያ የመጡ ማስመሰል፣ በተለየ ጊዜና ዓመተ ምሕረት የተነሱትን ዛሬ እንደተነሱ አድርጎ ማቅረብ (ጎንደር ጥምቀት ላይ የተነሣ ፎቶ ሰልፉ ላይ እንደተነሣ ተደርጎ ሲቀርብ እንዳየነው)፤ የወያኔው ባለስልጣናት ስም ያለባቸውን (ምሳሌ የዶ/ር ደብረ ጽዮን እና ኃ/ማርያም ፌስቡክ አካውንቶች) ነገር ግን በትክክል ያልተረጋገጡ የፌስቡክ ገጾችን እና ሌሎች ማንነታቸውን ለማጣራት የሚያስቸግሩ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ስብስቦችን «አካውንቶች» አምኖ በመቀበል የሚለጠፉት መልእክቶችን ተከትሎ መንጎድና ዋናውን አጀንዳ መዘንጋት ወዘተ፤
+++
ስለዚህ እነዚህ ጉድለቶች መሙላት ይቻል ዘንድ የአገራቸውን ጉዳይ በመከታተል ላይ ያሉ ወገኖች በሙሉ የሙያ ርዳታ ማድረግ ይገባቸዋል። አንዳንድ ጥቃቅን ስሕተቶች ሲገኙ ያንን በመያዝ የሕወሐት ቡድን የከፈተውን የፌስቡክ ጦርነት ከማገዝ ነገሮቹ እንዲታረሙ በማገዝ ኢትጵያውያኑን የሚዲያ ተቋሞች ማጠናከር ያስፈልጋል።

No comments:

Blog Archive