Sunday, October 2, 2016

አይረሴው የኦሮሞ «የምሥጋና ቀን» አያና ኢሬቻ እልቂት

(ኤፍሬም እሸቴ)፡- ዛሬ በዕለተ ሰንበት የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር በሚያከብረው የኢሬቻ በዓል ላይ እጅግ ብዙ ሕዝብ አልቋል። ቁጥሩ ከሰዓት ወደ ሰዓት እያሻቀበ በመሆኑ በእርግጠኝነት ይኼንን ያህል ነው ለማለት ጊዜው ገና ነው። እስካሁን ግን ከ175 ሰው በላይ (ከ360 በላይ ሚሉም አሉ) መሞቱ ታውቋል። የሞቱት አብዛኞቹ ወጣቶች ቢሆኑም ካገባች ገና አንድ ወር ያልሞላትን ሙሽራ (ወ/ሮ ሲፈን ለገሰን) ጨምሮ ወንዶችም ሴቶችም፣ ወጣቶችም፣ ገና ለጋ ልጆችም ተቀጥፈዋል። በሕይወት ቢተርፍም አደጋ የደረሰበት ብዙ ሺህ ሰው እንደሚኖር ይገመታል። 
በዓሉ የሚከበርበት «ሆራ አርሰዲ»
 ወዳጄ አዲስ ተስፋዬ ስለቦታው እንዲህ ይላል፡- «እሬቻ የሚከበረው ሆራ አርሰዲ በተባለው በተለምዶ ሆራ እየተባለ በሚጠራው የቮልካኖ ሐይቅ(crater lake) ውስጥ ነው:: ሆራ ሀይቅ ያለው ለጥ ያለ ሜዳ ላይ አይደለም:: ጉድጓዳ ነው:: ዙርያውን ገደል ሆኖ መሀሉ ላይ ሀይቁ አለ:: ወደ ሐይቁ ለመግባትም ሆነ ለመውጣት የሚያገለግሉ ሁለት በሮች አሉት:: አንዱ በራስ ሆቴል በኩል ሲሆን ሌላኘው በደብረዘይት እርሻ ምርምር በኩል ያለው ነው:: እሬቻ የሚከበረው ገደሉን በመውረድ ውሃው አጠገብ ነው:: ውሃው አካባቢ ያለው መሬት በቂ ስላልሆነ አብዛኛው ሰው የሚታደመው ገደሉ ላይ ነው:: ገደሉ ላይ ቆሞ ከታች ውሃው ዳር የሚካሄደውን ሂደት ይከታተላል::»

  
እንዴትና ለምን ሞቱ?
የሞቱት ወገኖች የሞታቸው መንሥዔ ሕዝቡ የሚያሰማውን የተቃውሞ ድምጽ መግታት የፈለጉት የሕወሐት/ኢሕአዴግ ወታደሮች በሕዝቡ ላይ በተኮሱት አስለቃሽ ጭስ በተፈጠረ መገፋፋት፣ ገደል ውስጥ እና ባህሩ ውስጥ የመግባት አደጋ እንዲሁም በጥይት ነው። ዝርዝር ጉዳዩ ወደፊት ቀስ በቀስ መገለጡ ስለማይቀር ሁሉንም እንደርስበታለን።
ሕወሐት በዛሬም የሕዝብ ፍጅት ልትመለስበት የማትችለውን ትልቅ የሰቆቃ መስመር ተሻግራለች። ሰሞኑን ባለሥልጣኖቻቸው ሲናገሩ እንደነበረው ትልቅ በጀት በመመደብ፣ ሚኒስትር በመቀያየር፣ አዲስ ስልት በመንደፍ ነገር ግን አገሪቱን እየመሩ ለመቀጠል የማይቻልበትን ትልቅ እርከን (ማይል ስቶን) አልፋለች። ከዚህ በኋላ እነርሱ አገር እያስተዳደሩ ሰላማዊ ሕይወት ይቀጥላል ብለው የሚያስቡ ከሆነ በእጅጉ ተሳስተዋል። ላይጠገን ተሰበረ እኮ።
ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት አደጋ በቢሾፍቱው «ሆራ አርሰዲ» ተከስቶ አያውቅም። ይህ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ጭፍጨፋ የተካሄደበት ጊዜ ነው። ሕወሐት (ራሷ በሠራችው ድራማም ቢሆን) ሐውዜንን የደርግ የጭካኔ ምልክት እንዳደረገችው እነሆ አሁን ደግሞ ኢሬቻ የወያኔ የጭካኔ መገለጫ፣ የኦሮሞ ሰማዕታት ሁሉ መታሰቢያ፣ የምሥጋናም የጸሎትም በዓል ይሆናል።
ወ/ሮ ሲፈን ለገሰ
 ብዙ ሕዝብ እንደሚመጣ ስለሚታወቅ ዝግጅት ማድረግ ይችሉ ነበር
በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የሚገለጥበት መድረክ ስለሚፈልግ በዚህ በዓል ላይም ብዙ ሰው እንደሚመጣ ለመገመት ብዙ ሊቅ መሆን አይጠይቅም። መንግሥት ቢኖረን ኖሮ ሕዝቡ ከመብዛቱ የተነሣ አደጋ እንዳይፈጠርበት (ክራውድ ማኔጅመንት) ዝግጅት ሊደረግ ይችል ነበር። ካድሬዎቻቸውን ንግግር እንዲያደርጉ ከመጨነቅ ይልቅ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ይተጉ ነበር።
ምን ያህል ሰው ተገኘ የሚለውን መልስ ለማግኘት ቀላል ባይሆንም በሚሊዮኖች ከሚገመት ቁጥር እስከ መቶ ሺዎች የሚደርሱ ሰዎች እንደተገኙ ሲዘገብ ነበር። ያንን ለሚያህል ቁጥር ቦታው እንደማይበቃ ይታወቃል። ይህ የሕዝብ ብዛት ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ ለመከላከል ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ምን ያደረገው ዝግጅት ነበር? የቢሾፍቱ አካባቢ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጨፌ ኦሮሚያ ድረስ ሉ ባለሥልጣኖች መልሳቸው ምንድነው?
የሕዝብ ቁጥር ብዛት ብቻ ሳይሆን ሰዉ እርስ በእርሱ የሚፈጥረው መጠጋጋት እና መጨናነቅ በቀላሉ የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል መገመት ይገባቸው ነበር። መድረክ አዘጋጅተው ፕሮፓጋንዳ ለመሥራት ከመጨነቅ ይልቅ ለዚህ ቅድሚያ ሊሰጡ ገባ ነበር። ይህንን አለማድረጋቸው ሳያንስ ሕዝብ ላይ መተኮስ፣ ማስደንበር፣ ግርግር መፍጠርና ሰውን ለአደጋ ማጋለጥ ትልቅ ወንጀል ነው። ተጠያቂው ማነው?

የእምነት በዓላትን ወታደራዊ «በአል» የማድረግ ችግር
ሕወሐት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው የሕወሐት ጦር የተቀደሱ በዓላት ላይ የሚያሳየው ድንበር ጥሰት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱ ነው። የበዓሉ ባለቤቶች ራሳቸው በፈቀዱት መልክ ሥነ ሥርዓታቸውን ማስከበር ሲችሉ ወታደሮች ለበዓላቱ በማይመጥን መልኩ አስከባሪ መስለው ሕዝቡንና በዓሉን በመበጥበጣቸው ሃይማኖታዊ በዓላቱ ወታደራዊ ዝግጅት ወደ መምሰል ሄደዋል። በጥምቀት፣ በደመራ፣ በእስልምና በዓላት ላይ ሁሉ ወታደር ከፊት አለማየት አይቻልም። በኢሬቻም የሆነው ይኸው ነው። ለብዙ መቶ ዓመታት እንዳደረግነው በዓላችንን ራሳችን እንዳናስተናግድበት እና እንዳንስታናገድበት የወያኔ እጅ ያልገባበት ቦታ ባለመኖሩ ሁሉንም ነገር አበላሽተውታል። ወታደራችሁን ከመስቀል አደባባያችን፣ ከጥምቀት በዓላችን፣ ከኢሬቻው፣ ከእስልምናው በዓል ብታወጡ ሕዝቡ እንደለመደው የራሱን ሥርዓት በራሱ መንገድ ማስተናገድ ይችል ነበር። መንፈሳዊ ቦታ እንኳን ለሕዝቡ ሰላም ብትሰጡት ምን ነበር?
እሬቻ የሄድኩ ጊዜ ....
ለእሬቻ ባህል እንግዳ አይደለሁም። አዲስ አበባ ብወለድም፣ ሆለታ ገነት ባድግም፣ ከሰላሌ ዘመዶቼ ወይም ከሜታ ዘመዶቼ ባህል በራሴ ጥረት ለመቅሰም ስሞክር ነው የኖርኩት። በራሴ አቅም ወንዝ የምታሻግር ኦሮምኛ ለምጃለሁ። አንዱ ወንድሜ እና አንዷ እህቴ «ጆሯቸውን ቢቆርጧቸው» እንኳን አይሰሙም ነበር። እህቴ አሁን በራሷ ጥረት ከእኔ በተሻለ መናገር እንደቻለች ስረዳ በጣም ገርሞኛል። የእናቴ አያት፡መንዜዋ ሴት ቅድመ አያቴ አልጋ ላይ ከዋሉ ደርሼ አይቻቸዋለሁ። ሴቷ አያቴ፣ የአባቴ እናት፣ ሰላሌ ትዳር የመሰረተችው ከአባይ ማዶ፣ ከጎጃም መጥታ እንደሆነ ሰምቻለሁ። ከሌላው ከሌላው ብሔረሰብ ከስንቱ እንደተቀየጥኩ እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው።
ብሔረሰቤ ይኼ ነው ልላችሁ አይደለም። ከሁሉ ከሁሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ነው ልቤ የሚሞቀው፤ አገሬ ኢትዮጵያ ናት ስል ዕንባ አይኖቼን ይሞላዋል። የአማርኛም ሆነ የኦሮምኛ ቀረርቶ ስሰማ እንደ ዘፈን ሳይሆን በደም ስሬ እንደሚወርድ እሳት ያቀጣጥለኛል። እንዲህ ነው የኖርኩት። ወያኔንም አምርሬ የምቃወማት ይኼንን ልትነጥቀኝ እንደመጣች ስለማውቅ ነው። እንግዲያውስ ከሆነማ ከኢትዮጵያ ጀግኖች ሁሉ ቁንጮ የልቤ ጀግና የትግሬው ራስ አሉላ እንግዳ (ራሱ አሉላ አባ ነጋ) ነው። ልጅ ስወልድ ስሙን አሉላ እንደምለው ገና 9 ክፍል ሳልደርስ ቃል ገብቼለትም ነበር። አሁንም ፍቅሬ ያንን ያህል ነው።

ይሁንና በእሬቻው ዕለት የተፈፀመውን ታሪክ ይቅር የማይለው ፍጅት ሳይ አንዲት ቀን እርሜን ቢሾፍቱ ከሆራው የሄድኩበትን አጋጣሚ አስታወስኩ። ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በምሠራበት ዘመን ያንን ባህል ለመዘገብ መሔዴ ትዝ አለኝ። በትክክል ካስታወስኩ፤ በዕለቱ የሰማሁት ዘፈንና ልመና ኦሮምኛ ብቻ እንዳልነበረ አይዘነጋኝም። የተለያዩ የአማርኛ ዘዬዎች ያሉባቸው ጭፈራዎች ይወርዱ ነበር። መነሻው የኦሮሞ ባህል ቢሆንም ሌላው ብሔረሰብም እንዴት እንደተቀየጠበት አይቻለሁ። ባህል ፖለቲካ ሲጫነው ሌላውን ወደ ውጪ ይገፋል እንጂ እሬቻው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆኖ ነበር። እነሆ በዚህ በወያኔ ፍጅት ባህል ድጋሚ ኢትዮጵያዊ ተደርጎ ታተመ። ከዚህ በኋላ፣ እሬቻ የወያኔ የዘር ፍጅት ሐውልት የሚቆምበት ብሔራዊ በዓል ነው። ብቻ ደግ ቀን ይምጣ።
ይህንን ጽሑፍ አዳብረን እና መረጃዎችን ጨምር እንመለስበታለን። 

ምሥጋና፡-
ፎዎዎችን የወሰድኩት ከአዲስ ተስፋዬ፣ ከአዳነ ግርማ እና ከደረጀ ሀብተ ወልድ ገጾች ላይ ነው።

No comments:

Blog Archive