Wednesday, October 12, 2016

የካህናት ሚና - በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ዙሪያ (ውይይት በአደባባይ ቃለ ምልልስ)

አገራችን ኢትዮጵያ በጥልቅ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ትገኛለች። በብዙ የአገራችን ክፍሎች ሕዝባዊ እምቢተኝነት በማየሉ ሕዝቡ አልገዛም በማለት ላይ ይገኛል። መንግሥት በበኩሉ ለሰላማዊ ጥያቄ አደባባይ የሚወጡ ዜጎችን ያለ ርኅራኄ ይገድላል። ወጣቶችን እና በተቃውሞ ቆመዋል ያላቸውን በሙሉ በመደብደብ፣ በማሰቃየት እና በግዞት መልክ ወደ ሩቅ ቦታ ወስዶ በማጎር ላይ ይገኛል። መንግሥት ሕዝቡ በምንም መልኩ የተቃውሞ ድምጽ እንዲያሰማ ባለመፍቀዱ የእሬቻን በዓል ለማክበር በወጡ ዜጎች ላይ አስለቃሽ ጢስ በመተኮስና ሕዝቡን በማስደንበር ብዙ ወገኖች ባህር ውስጥ በመግባት፣ ከገደል ውስጥ በመውደቅና በመረጋገጥ ሕይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል። ለጠፋው የሰዎች ሕይወት ተጸጽቶ ሕዝቡን ከማረጋጋት ይልቅም «ይህንን ያደረጉት ፀረ ሰላም ኃይሎች ናቸው» በሚል ሌላ ዙር ዘመቻ ከፍቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወገኖቻቸውን በሞት የተነጠቁ ቤተሰቦች ለምሥጋና ወጥተው ከመንገድ የቀሩ ዘመዶቻቸውን ሲቀብሩ ሰንብተዋል። ይህም ቁጥር በመንግሥት ግምት 54 ሲሆን በሌሎች ተቋማት ግምት ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠር መሆኑ እየተገለጸ ነው። ልብ የሚሰብረው ይህ አደጋ ከተፈጠረ በኋላ በመላ ኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ የተቀጣጠለ ሲሆን መንግሥት ሕዝቡን መግደሉን ቀጥሎበታል። ንብረቶችም በመውደም ላይ ይገኛሉ። ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት እሳት ሲሳይ በመሆንም ላይ ናቸው። ይህ አለመረጋጋት ሊቆም የሚገባው በቅድሚያ በመንግሥት በሳል አመራር መሆን ቢገባውም ሕወሐት የሚመራው የኢሕአዴግ አመራር በሚወስደው ጭካኔ የተሞላበት ርምጃ ነውጡ እየተባባሰ በመሔድ ላይ ይገኛል።
አለመረጋጋቱን አስመልክቶ ፓትርያርክ አባ ማትያስ ቋሚ ሲኖዶሱን ጠቅሰው ጸሎተ ምሕላና ሱባዔ ያወጁ ቢሆንም ሕዝቡ ትዕዛዙን ከቁብ ሳይቆጥረው ቀርቷል። የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባኤ የተባለው አካልም ተመሳሳይ የመረጋጋት ጥሪ ቢያቀርብም ለእምነት አባቶቹ ሕዝቡ ጆሮ ዳባ ማለትን መርጧል። ይህ የሚያሳየው ሕዝቡ የእምነት አባቶቹን እንደማያምንባቸውና ቃላቸውን ለመስማት እንደማይፈልግ ነው። ከዚህ ሁሉ አንጻር የካህናት አባቶች ሚና ምንድነው? የሚለውን ያድምጡ። 
አዘጋጅ፡-    ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ 
እንግዶች፡- እንግዶቻችን ቀሲስ አሸናፊ ዹጋ እና ቀሲስ ንዋይ ካሳሁን ናቸው። የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሎጅ ምሩቃን የሆኑት ሁለቱ እንግዶች በተለያዩ እርከኖች ቤተ ክርስቲያናችንን ያገለገሉና በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው። 
ውይይቱን በድምጽ ብቻ ለማዳመጥ
ክፍል አንድ - Click Here.
ክፍል ሁለት - Click Here.
ክፍል ሦስት - Click Here.

ውይይቱን በዩ-ቲዩብ/  Youtube ለመከታተል
ክፍል አንድ - Click Here.
ክፍል ሁለት - Click Here.
ክፍል ሦስት - Click Here

No comments:

Blog Archive