Friday, October 14, 2016

አንዲት ሚጢጢ ትልቅ ጥያቄ፡ በእንተ «ሐበሻ»

(ኤፍሬም እሸቴ)፡- ሚጢጢ ካሉ ትልቅ፤ ትልቅ ካሉ ሚጢጢነት የለም ይቺ ግን ሁለቱንም ናት። ሚጢጢ ስላት ትልቅ እየሆነች ብዙ አስቸግራኛለች። ይቺም «ሐበሻ» የምትባል ቃል/ስም ናት። ቀደም ያሉ የፈረንጅ ምሁራን «አቢሲኒያ» የሚሉት «አቢስ» ‘abyss’ ከሚል ደግ ትርጉም ከሌለው ቃል አመንጭተው ቢሆንም አረብኛውን ጨምሮ በግሪኮቹምና በሄሮግሊፊክስ ጽሑፎች ያለው ግና በቀይ ባሕር አካባቢ ያለ አካባቢንና ሕዝብን የሚመለከት ነው። የውጪ አገር አጥኚዎች እና ካርታ ሰሪዎች የዓለም ካርታ በሚሠሩበት ወቅት አሁን አገራችን የምትገኝበት አካባቢ እና አፍሪካን በገባቸው መንገድ ሲሰይሙ፣ ሲቀይሩ ኖረዋል። አገራችንን አቢሲኒያ ብለው በሰፊው ሲጽፉ መኖራቸው እሙን ነው። ይሁንና ኢትዮጵያውያን ግን ራሳቸውን «ኢትዮጵያውያን» በማለት ሲጠሩ ኖረዋል። ነገሥታቱም «ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» ይሉ ነበር እንጂ «የሐበሻ ንጉሥ» ማለታቸውን አንብቤ አላውቅም።

+++++++
የፈረንጆቹ «የሐበሻ ትርትክት» በተለይም በአውሮፓ የታሪክ ትምህርት አድርጎ ወደ አገራችን ከገባና ራሳችንን በዚያው ቅኝት መመለክት ከጀመርን ወዲህ ልክ እንደ ውጪዎቹ ካርታ ሰሪዎች «ሐበሻ የሆነና ሐበሻ ያልሆነ» ኢትዮጵያዊ የሚል ግንብ ሊገነባ ችሏል። በተለይም የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት አወቃቀር እና ታሪክ የሚያስተሐቅሩ ጎሳ ዘመም ታሪክ አጥኚዎች «ሐበሻ» የሚለውን ቃል የታሪክ ትርክታቸው ምሶሶ አድርገውታል። ሐበሻ የሚባል ቅኝ ገዢ እንደሰፈረባቸው አስመስለው «እኛ እና እነርሱ» የሚለውን ዳይኮቶሚ መሬት ሊያሲዙት ችለዋል። 
ያንን የተቃወሙ የመሰላቸው ሰዎች ደግሞ «የኔ ሐበሻ» የሚለውን ዘፈን እጅግ ከፍ አድርገው ከፍተውታል። አብዛኛውም ነገር ብሽሽቅ እንጂ መማማርና መነጋገር ስላልሆነ አንዱ አንዱን በአንዲት ቃል መውጋት ሲፈልግ «ሐበሻ» ይመዛል። ከሰሞኑ፤ ወዳጃችን ጃዋር ባደረጋት ያቺ «የቻርተር» ንግግሩ በዲፕሎማሲው ረገድ እኛና እነዚህ ሐበሾች ስንወዳደር፣ እኛ እንደ ዱኩላ እየፈጠንን ነው እነርሱ ገና እንደ ኤሊ እየዳሁ ነው ብሎ ለማነጻጸሪያ መውጊያ ብረትነት «ሐበሻ» ተጠቅሞባታል። (ያለውን ቃል በቃል ለማስቀመጥ እነሆ «ሌላ የድፕሎማሲው ሥራ ለጉድ እየተሠራ ነው። ኢንሬዲብል! እኛንና ሐበሾቹን አነጻጽራችሁ ብታዩ፥ እነሱ እንደ ኤሊ እየተንፏቀቁ ነው። እኛ ደግሞ እንደ ድኩላ ፈጥነን እየሮጥን ነው። በዚህ ልትኮሩ ይገባል።»)
++++++++
የታሪክ ምሁራን አንድ ቀን የዚህችን ቃል ምንነት አምልተውና አስፍተው ሲያቀርቡልንና ከመበሻሸቂያነት ይልቅ መማማሪያ ሲያደርጉልን በርግጥም ሰከን ብለን እንግባባበት ይሆናል። ዋናው ምግብ (ራት») እስኪደርስ ማዳረሻ ቆሎም ቂጣም እንደሚቀርበው፣ የታሪክ ምሁራን ዋናውን ምግብ እስኪያቀርቡ እኛ ደግሞ ባለችን አቅም ሰፋ አድርገን እንመለስበት ይሆናል።

ይቆየን፣
አነ ፀሐፍኩ ኤፍሬም ኢትዮጵያዊ፤


2 comments:

yirgalem said...

በዚህ ወቅት ይሄንን ሀሳብ ማንሳትህ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል። ጃዋር መሐመድ ”እኛ እና እነዚህ ሀበሾች“ በማለት ሲናገር ውስጡ ሚጋጭበት ይመስለኛል፤ ምክንያቱም እሱም ግማሽ ጎኑ ”ሐበሻ“ ብሎ ከፈረጃቸው ጋር ስለሚዛመድ። ያው ፖለቲካ ሆኖበት ደጋፊዎቹን ላለማጠት እነሱ የሚያስቡን የተናገረላቸው መስሎም ተሰምቶኛል። ይህም ሆነ ያ ግን የራሱን ሀሳብ ማራመድ መብቱ ነው።
ታሪካችን ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ብዙ ተመራማሪዎች በገባቸው መጠን ብዙ ተብሎዋል። ተጽፎዋልም። የሕዝብ ታሪክ ሲጻፍ መረጃ እና ማስረጃዎች ማጣቀስ ያስፈልጋል። እንኳን የሕዝቦች ታሪክ ይቅርና የአንድ ግለሰብ ታሪክ ለመጻፍ እንኳን ስለ ግለሰቡ ብዙ የመረጃዎች ምንጮች ያስፈልጋል። አሁን በእኛ ዘመን ታሪክ እንደ ድርሰት ያለ ምንም መረጃ እና ማስረጃዎች እየተጻፉ ናቸው። የታሪካችን ታሪክ ብለው የጻፉም አሉ።
የኢትዮጵያ ታሪክ የጻፉ የታሪክ ምሑራን “የሁንም ሕዝቦች እና ሀይማኖቶች ታሪክ አልተካተቱም” በማለት የሚተቹ የተለያየ አመለከከት ያላቸው ሰዎች ሲናገሩ እንሰማለን። ቀደምት በተጻፈው ታሪክ ያረኩ አንዳዶቹ በራሳቸው አመለካከት ብቻ ማስረጆዎች ሳያካትቱ ታሪክ ብለው የጻፉም አሉ። ማስረጃ እና የመረጃ ምንጮ ተጠቅመው ቢጽፉ መለካም ነው፤ ተቃውሞ የለኝም።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው በመግቢያው ላይ መረጃዎች እና ማስረጃዎች በማጣቀስ [ኢትዮጵያ] የሚለው ስያሜ አመጣጥ በደንብ አድርገው ገልጸውታል። አብራርተውታልም። ብፁዕነታቸው ሲያብራሩ “ኢትዮጵያ በጥንት የግብጽ ቋንቋ ጱንጥ፣ ቶ፣ ኔቶር፣ ኩሽ እየተባለች ትጠራ ነበረ” በማለት ጽፈዋል።
ብፁዕነታቸው መጽሐፍ ቅዱስ እና የተለያዪ ጥንታውያን የግሪክ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደማስረጃ እያጣቀሱ [ኢትዮጵያ] የሚላውን ቃል አመጣጥ እንደሚከተለው አብራርተውታል።
“ጱንጥ የሚለው ቃል በብሉ ኪዳን መጻሕፍት፦
1/ ፉጥ ከሚለው ስም ጋር ይመሳሰላል። ቶ፣ ዮቶር ማለትም ሀገረ እግዚአብሔር ማለት ነው ይላሉ። ሙሴ ብሉ ኪዳን ሲጽፍ ይህችኑ አገር [የኩሽ ምድር] እያለ የጻፈው በግብጽ ተወልዶ ያደገ እንደመሆኑ መጠን የግብጻውያን ቋንቋ ያውቅ ስለነበረ ነው እንጂ፤ ኩሽ የሚለው ቃል የእብራይስጥ ቃል አለመሆኑ ታውቋል። ኢትዮጵያ የኩሽ ምድር ለመባል የበቃችበት ዋና ታሪካዊ ምክንያት፤ የካም የመጀመርያ ልጅ የኩሽ ዘሮች ስለሰፈሩባት ነው። ይህችው ሀገር በሌላ አጠራር፦ [የሳባ ምድር] አንዳንድ ጊዜም [አቢሲኒያ] እየተባለች ትጠራለች፤ ምናልባትም ይህ ስያሜም የተገኘው እነዚሁ የኩሽ ልጆች ሳባ እና አቢስ (ሰብታ) ስለሰፈሩባት በስማቸው አስጠርተዋታል ማለት ነው።
2/ በሳባ የሳባ ምድር፥ በሰብታ (በአቢስ) አቢሲኒያ እየተባለች ለብዙ ዓመታት ቆይታለች። ዐረቦች ግን አቢሲኒያ የሚለው ስያሜ [ሐበሽ] ብለው ድብልቅልቅ ውጥንቅጥ ለማለት ይቃጣሉ። ነገር ግን ምንጭ የለውም። ምዕራባውያን አሁንም አቢሲኒያ እያሉ ይጠሯታል።
3/ በ3600 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት በየመን ይኖሩ የነበሩ ከነገደ ሴም የተከፈሉ ነገደ ዮቅጣን በባብ እልመንደብ (የመከራ በር ማለት ነው) በኩል ገብተው ሰፈሩባት። በዚህች አገር ከሚኖሩ የኩሽ ዘሮች ጋር እየተጋቡና እየበረከቱ ሄዱ። በዚያን ጊዜ ይህችን አገር ምድረ አግዐዚት፦ ምድረ አግዐዝያን፥ ነፃ አገር ነፃነት ያላቸው ሰዎች መኖርያ ብለው ጠሯት። በመጨረሻ ለዚች አገር የተሰጣት ስያሜ [ኢትዮጵያ] የሚል ነው። በሀገራችን እንደሚተረከው ኩሽ ሁለት ስም ነበረው። ሁለተኛው ስሙ [ኢትዮጲስ] ይባላል። አቅኚዎቹ ባባታቸው ስም ይቺን አገር [ኢትዮጵያ] ብለዋታል፤ እነሱም ኢትዮጵያውያን ይባላሉ እየተባለ ይተረካል። አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ፦ [ኢትዮጵያ] የሚለው ቃል ከግሪከኛ የተወረሰ ነው [ኤቶስ] ዋዕይ [ኦፕ] [ሲስ]፦ ገጽ አርአያ ማለት ነው። እነዚህ ሁለት ቃላት ሲጣመሩ [ኤቴኦፒያ] ወይም [ኤቲኦፕስ] የሚል ቃል ይወጣዋል፤ ይህም እንደመጀመርያው [ኢቲኦፒያ] ቢል የአገራችን ቆላነት ያመለክታል። ቆላ በረሃ፤ የዋይ፣ የትኩሳት አገር ማለት ነው። እንደ ሁለተኛው [ኤቲኦፕስ] ቢል ግን የሕዝቧን ምንነት ያመለክታል። በዋዕየ ፀሐይ ፊት የበለዘ፣የጠቆረ፣የበረሃ፣የቆላ ሻንቅላ ማለት ነው። በሆሜር መጽሐፍ ደግሞ ቀዪን ወይም ኢትዮጵያ ብሎት ስለሚገኝ፦ [ኢትዮጵያ]ማለት ቀይ የቀይ ዳማ ቀለም ያለው ሕዝብ ማለት ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያውያን አባት ኩሽ በሞተ በ2450 ዓመት በ284 ከጌታ ልደት በፊት፤ መጽሐፍተ ብሉያትን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ የመለሱ ሰባው ሊቃውንት ሙሴ ፦ [ኩሽ] እያለ በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን የጻፈውን ኢትዮጵያውያ በሚል ቃል ለውጠውታል።“
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ከመጽሐፋቸው ግርልጌ(fotnote) የተጠቀሟቸው ምንጮች ጠቅሰዋል። አሁን በዚህ ዘመን ጎልቶ እየወጣ ያለው [ሐበሻ] ወይም በአረቦቹ አጠራር [ሐበሽ] የሚለው ቃል ታሪካዊ አመጣጥ ምንጭ እንደሌለው በዚህ መጽሐፍ ላይ ተገልጾዋል። ግን ይህ ማለት ዐረቦቹ ለኢትዮጵያ የሰጣት ትርጓሜ መሆኑን መገመት ይቻላል።
በአሁን ወቅት እነ ጃዋር መሐመድ እና ሌሎችም የኦሮሞ ተወላጅ ሙስሊሞች የዐረቦቹን ስያሜ አሰጣጥ[ሐበሽ] የሚለውን ቃል ተቀብለው የራሳቸውን አጀንዳ እና አመለከከት እያስፈጸሙ ይመስለኛል። ይህንን በሀሳብ ወይም በአመለካከት ደረጃ ይዘው መንቀሳቀስ መብታቸው ነው። እኔም ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን ከእውነታ ጋር እነሱን ተከራክሮ የሚያሸንፍ ምሁራን ያስፈልጉናል። ዐረቦቹ የራሳቸውን ዓላማ ለማስፈጸም ማለትም የምሥራቅ አፍሪካዋ በእስልምና ሕግ የምተደዳደር አገር ለመፍጠር አዳዲስ ታሪኮች ከመፍጠር ወደ ኋላ የሚሉ አይመስለኝም። ያው ዐረቦቹ እና ቱርኮች የኢትዮጵያ የቀደሙት ነገስታት ኦርቶክስ ክርስቲያን ስለነበሩ እና ክርስትናን ለመስፋፍት ይጥሩ ስለነበር ኢትዮጵያ የእነሱ ተቀናቃኝ አድርገው ያያቷል። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን ለማዳከም ብዙ ሞክረዋል። ክርስቲያኑ የኦሮሞ ተዋላጅ ምሁራን ግን ይህንንታሪክ ጠንቅቀው ያውቃሉ የሚል እምነት አለኝ። የእነዚህን ሰዎች አስተሳሰብም ይቀበሉታል ብዬ አላምንም። በዚች ወሳኝ ጊዜ እውነትን የያዙ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን ታሪካዊ ስህቶቶች እንዳይሰሩ ነቅተው መጠበቅ እና ተከራክረው ማሸነፍ አለባቸው ብዬ አምናለው። በኋላ ጊዜው ካለፈ ” ጀብ ከሄደ ውሻ ጮኸ“ እንዳይሆን በንቃን የመስሪያ ጊዜ አሁን ነው።
ምንጭ፦ [የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ] አዘጋጅ አባ ጎርጎርዮስ (MA)

Anonymous said...


ሰላም ጤና ይስጥልኝ ወንድም ዲያቆን ኤፍሬም። "ሀበሻ" የሚለው ቃል "ሀበሻ" ተብሎ ሳይሆን "ሕብስት" ተብሎ በጥንታዊ የአለት ጽሁፍ (inscription) ተጽፎ በአክሱምና ጥንት ሑመራ ትባል በነበረው በአሁኗ የመን ይገኛሉ። በየመን የሚገኘው አንዱ ጽሁፍ በጎሳዎች መካከል ሰለነበረ ግጭት የሚያወራ ይመስላል። "ሳባን ለማጥቃት ሕብስት የረዳውን ሰመረን እና ሑመራን አገዘ" የሚል ነው። ሳባም፣ ሕብስትም፣ ረዳም፣ ሑመራም የጎሳ ስሞች የነበሩ ይመስላል። በአክሱም የሚገኘውን ደግሞ ንጉሥ ኢዛና የሚባል ሰው እንደፃፈው ወይም እንዳፃፈው ጽሁፉ ይናገራል። በግእዝ የተጻፈው እንዲህ ይላል። "ኢዛና፡ ንጉሠ፡ አክሱም፡ ወሑመራ፡ ወረዳ፡ ወካሱ፡ ወሳባ፡ ወሰላሓኑ፡ ወጸርድ፡ ወሕብስት፡ ወበጌ፡ ንጉሠ ነገሥት፡ ወለደ፡ ለመሐራም፡ ዘይእትመውእ፡ ለፀረ፡ አፅራሩም፡ ሕዝበ፡ በጌ፡ ወፈኑወነ፡ አኀዎነ፡ ዘዐሰንህ፡ ወአድፈሃ የፀበአዎሞ።"

በጌ የሚለው የበጌምድርን ህዝብ ነው። በኢዛና ጽሁፍም ላይ ስናይ ሕብስት ተበሎ ነው የተጻፈው፡፤ ስለዚህ ሀበሻ የሚለው ቃል ሕብስት የሚለው ቃል ተወላግዶ (corrupted ሆኖ) እነደሆነ መረዳት እንችላለን። በዛ ዘመን የተጻፉ ሌሎች ጽሁፎች ደግሞ ሕብስትንና ካሱን (ኩሸን) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አክሱምን እያቀያየሩ ሲጠቀሙ እናያለን። ይህ የሚያሳየው ሕብስትና ካሱ (ኩሽ) የተራራቁ እነዳልሆኑ ነው። እንዲያውም ካሱና ሕብስት ለኦሮሞ የቀረበ የዘር ዝምድና እንዳላቸው ነው የምናየው። ምክንያቱም ኦሮሞ የኩሽ ዘር ነውና። የጃዋር ትምህርት ትኩረቱ ማበጣበጥና ማለያየት ስለሆነ እውነትና መረጃዎች ከነሱ ቤት ቦታ ያላቸው አይመስልም እንጂ ይህ መረጃ ሊያስተምራቸው ይችል ነበር።

በነገራችን ላይ የመን፣ ሰንዓ፣ አደን ወዘተ (ጥንታዊ የሆኑት የየመን ከተሞች ስም በሙሉ) የግእዝ ቃሎች እንደሆኑ ታውቃላችሁ? እንኳን ሌላ ኮረብታወችም ሳይቀር እስካሁን የግእዝ ስማቸውን እንደያዙ ይገኛሉ። ከዐረብ ወረራ በኋላ የተገነቡ ከተሞች ግን ስማቸው ዐረብኛ ነው።

ኃ.ሚ.

Blog Archive