Monday, October 17, 2016

ፍርሃት ምንን ይወልዳል?

(ኤፍሬም እሸቴ)፡- ኒቸ የተባለው የጀርመን ፈላስፋ ስለ ፍርሃት በተናገረበት ተጠቃሽ ጥቅሱ «ፍርሃት የሥነ ምግባር እናት ናት፤ Fear is the mother of morality.» ይላል። ምን ማለቱ እንደሆነ ለመተንተን የፍልስፍና ተማሪ መሆን ስለሚጠይቅ ለማብራራት ይከብደኛል። ሃይማኖትን የፍርሃት ልጅ አድርጎ ለማቅረብ የፈለገ ቢመስለኝም ለመደምደም ግን አልችልም። ይልቅ እርሱ «ፍርሃት ሥነ ምግባርን ትወልዳለች» ሲል እኔ ደግሞ በልቤ «ፍርሃት የጭካኔ እናት ናት፣» ወይም «ፍርሃት ጭካኔን ትወልዳለች» ብዬ አሰብኩ።

የፈሪ ዱላው ዘጠኝ ነው ይባላል። የፈሪ በትር ያምማልም ተብሏል። ጅብ አህያን ማደኑና መብላቱ የተለመደ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን አህያ ከፍርሃት ብዛት የጅቡን አንገት በጥርሱ ነክሶ የሚገድልበት ጊዜ አለ። በገጠር ብዙ ጊዜ ሲነገር ሰምተናል። የሚገርመው ግን አህያው ያነቀውን ጅብ ከገደለም በኋላ ሞቷል ብሎ ስለማያምን ሕዝብ ተሰብስቦ በብዙ ችግር ነው ከአፉ ላይ የሚያስለቅቁት። ጅቡን ከአፉ ከጣለ በኋላ በሚያስደንቅ ፍጥነት አካባቢውን ጥሎ ይጠፋል። አሁንም ጅቡ የሚደርሰበት እየመሰለው። ፍርሃት ይህንን ሁሉ ያደርጋል።
አንዳንድ ጊዜ፣ አንዳንድ ሰዎች በሌሎች ላይ የሚያደርጉትን የጭካኔ ተግባር ስትመለከቱ ውስጣቸው የነገሰው ፍርሃት እንጂ ድፍረትና ጀግንነት እንዳልሆነ ትረዳላችሁ። ጀግንነት ከጭካኔ ይልቅ ከትህትና እና ከይቅርባይነት ጋር ደባል መሆን ይመቻታል። ፍርሃት ደግሞ ከነ ትዕቢት፣ ከነ ጭካኔ፣ ከነኩራት ጋር ወዳጅ ናት። ውጤቷም ውድቀት ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን «ሰው ሳይወድቅ በፊት ልቡ ከፍ ከፍ ይላል፥ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።» (መጽሐፈ ምሳሌ 1533) ያለውን ማስታወስ ነው።
ፍርሃት የሚመነጨው አንድም የሚፈሩትን ነገር ጠንቅቆ ካለማወቅ ይሆናል። የተለያዩ የተፈጥሮ ክስተቶች ያስፈራሉ። ጎርፍ፣ እሳት፣ ዝናም፣በረዶ፣ ጫካው፣ አራዊቱ ሁሉ ያስፈራሉ። ነገር ግን የሰው ልጅ እያንዳንዳቸው ምን እንደሆኑ ጠንቅቆ ስላወቃቸው ፍርሃቱን አሸንፎ ይኖራል። ጎርፉን ይገድበዋል፣ እሳቱን ያጠፋዋል፣ ዝናሙን ይጠለለዋል፣ በረዶውን ይንሸራተትበታል፣ ጫካውን ይንሸራሸርበታል፣ እንስሳት አራዊቱን በአጥር ቀጥሮ ሲመለከታቸው ይዝናናል። ሰው የተፈጥሮ ጌታ ሆኖ ይኖራል።
ሰው ትልቁ የሚፈራው ሌላው ነገር ሌላውን ሰው ነው። በተለይም የማያውቀውን ፀጉረ ልውጥ ሰው እና ሰዎች ሁሌም ይፈራል። በምንኖርበት በአሜሪካ እንኳን ከሶሪያ የሚመጡ ስደተኞችን በተመለከተ ያለውን የአሜሪካውያን ፍርሃት ስንመለከት የሰው ልጅ የማያውቀውን ሰው እንዴት እንደሚፈራው ጥሩ ማሳያ ይሆነኛል። በአገራችንም እንዲህ ያለ ፍርሃት ከጊዜ ጊዜ በመስፋፋት ላይ ነው። አንዲት ትንሽ አገር ላይ ተቀምጠን አንድኛችን የአንድኛችንን ታሪክ ጠንቅቀን ባለመረዳታችን ምክንያት (ሰዎች እንድንፈራራም ስለፈለጉ) የተለየ ቋንቋ የሚናገረውን ሌላ ዜጋ በፍርሃት በመመልከት ላይ እንገኛለን። ለፍርሃት መድኃኒቱ መተዋወቅ ነው። ቀርበን እንፈታተሽ። እንለማመድ። ፍርሃት ይወገድልናል። የሚያስፈራን ነገር ተራ ስሜት ይሁን ወይም በርግጥም አስፈሪ ነገር ይኑረው ማወቅ የምንችለው ቀርበን ስናውቅ ብቻ ነው። አለበለዚያ ፍርሃታችን ያልሆነ ውሳኔ ብሎም ስሕተት ውስጥ ሊከትተን ይችላል። ታሪክ እንደሚነግረን በፍርሃት ብዙ በደል ተፈጽሟል።
እና ፍርሃት ምንን ይወልዳል ጎበዝ? «ጭካኔን» ነው መልሴ።

ይቆየን፣

1 comment:

Anonymous said...

ሰላም ወንድሜ ዲያቆን ኤፍሬም። የጀርመኑን ፍሬዴሪክ ኒችን ከትህትና ጋር በጣም በለጥከው። ስሜት የሚሰጠው ያንተ ትንታኔ እንጂ የሱ አይደለም። እግዚአብሔር ያገልግሎት ዘመንህን ያርዝምልን።

ኃ.ሚ.

Blog Archive