Friday, November 18, 2016

የአገሬ ልጆች ሆይ፡- ቁልፉ ያለው ከታሪክ ላይ ነው፤ It's the history, stupid.

ቢል ክሊንተን ለ1992 ፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ የተጠቀሙበት የምርጫ መፈክር ሁሌም የሚጠቀስ ትልቅ ሐሳብ ነበር። በወቅቱ በአገረ አሜሪካ ስለ ነበረው ዋና ጉዳይ (የኢኮኖሚ ጉዳይ) በአጭር አገላለጽ ያስቀመጡበት መሪ-ቃላቸው ነው። «ዋናው ነገር የኢኮኖሚው ነገር ነው» ለማለት በአጭሩ «ኢት ኢዝ ዘኢኮኖሚ፣ ስቱፒድ» (It's the economy, stupid) ማለትን መርጠዋል።

በአገራችን ያለውን ዕለት ተዕለት የሐሳብ ፍጭት እና ጦርነት ስመለከት እና ይህንን ሁሉ ምስቅልቅ በአንድ ሐረግ መግለጽ ስፈልግ ከቢል ክሊንተን የምርጫ መፈክር አባባሉን መኮረጅ ያምረኛል። እናም እኮርጃለሁ። «ኢት ኢዝ ዘሂስትሪ፣ ስቱፒድ» (It's the history, stupid) እላለሁ። የሀገራችን ዋና መግባቢያም መለያያም የታሪክ እና የታሪካችን እንዲሁም ታሪኮቻችን የሚተረኩበት ሁኔታ የታሪክ ፀሐፊዎቻችን እና የተራኪዋቻችን ነገር ነው። ቁልፉ እዚያ ላይ ነው። «ዋናው ነገር የታሪክ ነገር ነው»።

ሕወሐት ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ዋና ኢላማ ያደረገው ይህንን የታሪክን ዋልታ መሆኑ አለነገር አይደለም። ሕወሐት ብቻ ሳይሆን እንደርሱ ያሉት ጎሳ ዘመም ድርጅቶች በሙሉ ዋና ዒላማቸው ታሪክ መከለስ እና አዲስ ታሪክ መትከል ነው። ዋናውን ብልት አግኝተውታል።

ሕወሐት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የታሪክ ክፍል የዘጋው በአጋጣሚ ወይም እነርሱ እንዳሉት «ተማሪ ስለጠፋ» ብቻ አይደለም። ታሪክ አጥኚ ካለ ታሪክ ከላሾች ችግር እንደሚገጥማቸው ስለሚያውቁ ነው። ስለዚህም በዚህ 25 ዓመት ውስጥ የተወለዱ፣ ያደጉ፣ የተማሩ ልጆች (አሁንማ አድገዋል) አብዛኞቹ ታሪክ አያውቁም፤ አልተማሩም፣ እንዳይማሩም ተደርገዋል ባይ ነኝ። ታሪክ እንዲያጠኑ አልተበረታቱም። በዘመነ ሕወሐት ተወልደው ለሕወሐት ዋነኛ ተቃዋሚ የሆኑት ወጣት ልጆችን በሙሉ ልብ ብለን ከተመለከትናቸው በራሳቸው ታሪክ ለማንበብ እና ዓይናቸውን ለመግለጥ የቻሉ ልጆች መሆናቸውን እንገነዘባለን። የእነርሱ የዕድሜ አቻ የሆኑ ታሪክ ያላነበቡቱ ግን «ፖለቲካ ውስጥ አትግቡ» እያሉ ዳር እንደቆሙ ናቸው። የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ይህንን ሁሉ መከራ የሚቀበሉት ገና በለጋ ዕድሜያቸው መሆኑን ልብ ይሏል።

ለአገራችን ችግር መድኃኒት የምናገኘው የታሪክን ነገር መፍትሔ ስንፈልግለት ነው። ስለታሪካችን ያለ ንዴት፣ ያለ መሰዳደብ እና ያለ መደባደብ መነጋገር የቻልን ቀን የችግራችን መቅድም ላይ ደረስን ማለት ነው። አጼ ምኒልክ እና ጎበና፤ አጼ ዮሐንስ እና ቴዎድሮስ የብዙዎቹ ንትርኮቻችን ዋልታዎች የሆኑት እኮ አለነገር አይደለም። አሁን ደግሞ ደፈርና ገፋ ብለን ወደ 16ኛው መ/ክ/ዘመን መዝለቅ ጀምረናል። ዞሮ ዞሮ በታሪክ ትብታብ ውስጥ እየዳከርን ነው።

ወደድንም ጠላንም ሁላችንም የታሪክ እስረኞች ነን። ታሪክን አስረን ያስቀምጥነውም እኛው ነን። ተተብትበናል። James Baldwin/ጄምስ ባልድዊን፤ ከ100ዎቹ ምርጥ የአሜሪካ ልቦለድ ያልሆኑ ሥራዎች ምርጥ ዝርዝር ውስጥ በገባውና ተጠቃሽ በሆነው መጽሐፉ «ሰዎች በታሪክ ተጠላልፈው ታስረዋል፤ ታሪክም በሰዎች ውስጥ ተጠላልፎ ታስሯል፤ People are trapped in history, and history is trapped in them" ያለው አለነገር አይደለም። («Notes of a Native Son»)።

ምን ይሻላል ጎበዝ? ስለ አገራችን ታሪክ ሀ ብሎ ጀምሮ ማወቅ ለሚፈልግ አንድ ኢትዮጵያዊ/ት፣ ማንበብ ያለበትን መጽሐፍ ጠቁሙ ብትባሉ ከየት ትጀምራላችሁ? ከየት እስከ የት ያንብብ? ችግራችን እኮ ሌላ ምንም አይደለም ወዳጆቼ ያገሬ ልጆች፡- It's the history, stupid.

No comments:

Blog Archive