Tuesday, November 22, 2016

Thanksgiving የምሥጋና በዓል፣ በዓለ አኮቴት

ዛሬ “Thanksgiving” ላይ ቆሜ ስለዚህ በዓል ለብዙ ጊዜ ልጽፈበት እየፎከርኩ አለማድረጌን እየወቀስኩ ጥቂትም ቢሆን ልልበት ወሰንኩ። ምናልባት የፈረንጅ በዓል ስለሆነና ገና ስላልተዋሐደኝ ባዕድ ሆኖብኝ ይሆን እንጃ በተከታታይ ሦስት ዓመታት ብዕሬን አንስቼ ሳልፈጽመው ቀርቻለኹ። ዘንድሮስ አይሆንም ብያለኹ። በተለይ ለረዥም ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን በሐላፊነት ሲመሩ የነበሩትና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ “እኛ ልመና እንጂ ምስጋና አናውቅም፤ ማመስገን ያስፈልገናል” ይሉት የነበረው አባባላቸው የበለጠ አበረታቶኝ የግል ሐሳቤን ለመጠቆም ደፈርኩ።
“Thanksgiving” ወይም በአማርኛ “የምሥጋና በዓል” ወይም ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “በዓለ አኮቴት” ያሉት በዓል ከእንግሊዝ አገር በ17ኛው መ/ክ/ዘመን በስደት ወደ አሜሪካ የመጡ መጻተኛ እንግሊዞች ማክበር የጀመሩት፣ በፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሺንግተን ብሔራዊ በዓል ተደርጎ የተደነገገ በኖቬምበር ወር በአራተኛው ሐሙስ ላይ የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ በተለያየ ዘመን በተለያዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች ሲከበር ቆይቶ ከ1941 ጀምሮ የአሜሪካ ኮንግረስ የኖቬምበር  በአራተኛው ሐሙስ ብሔራዊ ክብረ በዓል ሆኖ እንዲከበር የወሰነበት በዓል ነው።
በዓሉ የቤተሰብ በዓል ነው። አዳሜ ተሰብስቦ “ተርኪ” የተባለውን ባለ ኩልኩልተ-ረጅም ዶሮ መሳይ ወፍ በማረድና በመጥበስ እንዲሁም በአንድ ገበታ ዙሪያ ተሰብስቦ በመመገብ ይከበራል። በዋዜማ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሁለት ተርኪዎችን ከመጠበስ ነጻ የመልቀቅ ሥርዓት የሚፈጽም ሲሆን ለሕዝቡም ንግግር ያደርጋል። በበነጋውም ሁሉም አሜሪካዊ እምነት ሳይለይ ፈጣሪውን ያመሰግናል። የተለየ የአንድ እምነት በዓል ባለመሆኑም አይሁዱም፣ ክርስቲያኑም፣ እምነት የለሹም፣ ሁሉም ሁሉም በየቤቱ ያከብረዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያኑን በተመለከተ በአዋቂዎቹ ዘንድ ሳይሆን እዚሁ አገር ተወልደው በሚያድጉ ልጆቻችን ዘንድ በዓሉ ትልቅ ትርጉም አለው። ወላጆች ግን ገና ና ፋሲካውን እንጂ እንዲህ ያለውን የፈረንጅ በዓል ከቁብ አንቆጥረውም። በተጨማሪም በዓሉ በአብዛኛው “የገና ጾም” ወይም ጾመ ነቢያት በምንው ጾም ላይ የሚውል በመሆኑ ብዙም ትኩረት አይደረግበትም። በተወሰኑ ዓመታት፣ ልክ እንደ ዘንድሮው ጾሙ ከመግባቱ በፊት ባለው ሐሙስ ላይ ይውላል። ምናልባት ያን ጊዜ የምግቡ ጉዳይ ይነሣ ይሆናል።
እኛ ኢትዮጵያውያኑ የምናመሰግንባቸው ብዙ በዓላት ቢኖሩንም በተለየ መልኩ “የምስጋና በዓል” የምንለው የተለየ በዓል የለንም። “ድሮስ በዓል ያለ ምስጋና ይከበራል ወይ?” ብሎ የሚጠይቅ ቢመጣ “አዎ በየበዓሎቻችን ፈጣሪያችንን እናመሰግናለን” እላለኹ። በኦሪቱም ሕዝበ እስራኤል በዓለ ሠዊት (ዘኁ. 28፤26፣ ዘጸ. 34፤22) በሚባለው በዓል ሰብላቸውን ሰብስበው፣ አሥራቱን በኲራቱን ካስገቡ በኋላ ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ በዓለ መጸለት ወይም የዳስ በዓል (ዘሌ.23፤39-44) በሚባለው ደግሞ በየሰባት ዓመቱ አንድ ጊዜ ዳስ በመሥራት እና በዳስ ውስጥ በማደር ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበት እና በየመንገዱ ያደሩበትን እያከበሩ አምላካቸውን ያመሰግኑ ነበር በዚያ እኛም እንመስላቸዋለን።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጸሎት ምሥጋና ዐቢይ ክፍል ነው። ወደ ቅዳሴ ከመግባቱ በፊት ካህኑ በሚያደርሰው “ወካዕበ ናስተበቊዕ ለንግሥተ ኲልነ” ብሎ ለእመቤታችን፣ ብሎም በጸሎተ ኪዳኑ “ለከ እግዚኦ ለገባሬ ኲሉ ለዘኢታስተርኢ አምላክ ንሰፍሕ ነፍሰነ። ወስብሐተ ዘነግህ ንፌኑ ለከ እግዚኦ ለጥበበ ኲሉ ሣህል አምላክ ሣራሪሃ ለነፍስ። ንሴብሐከ ለዘእምቅድመ ዓለም ተወልደ እምአብ፣ ቃል ዘበሐቲቱ በቅዱሳኒሁ ዕሩፍ፣ ኪያከ ዘትሴባሕ ስብሓታት ዘኢያረምም ወእምሠራዊተ ሊቃነ መላእክት። አቤቱ ሁሉን ለፈጠርህ ለማትመረመር አምላክ ለአንተ ሰውነታችንን እናስገዛለን፣ አቤቱ የነግህ ምስጋናንም እናቀርብልሃለን። የሁሉ ዕውቀት ኃያል የምትሆን፣ ይቅርታህ የበዛ አምላክ ነፍስን የፈጠርሃት፣ ከዓለም አስቀድሞ ከአብ የተወለድህ አንተን እናመሰግንሃለን” (ጸሎተ ኪዳን) እያለ ለጌታ ምሥጋናውን ያቀርባል። በቅዳሴውም “አእኲትዎ ለአምላክነ፣ አምላካችንን አመስግኑት” ሲል ሕዝቡ “ርቱዕ ይደሉ፤ እውነት ነው ይገባዋል” እያ በጋራ አምላካቸውን ያመሰግናሉ። ምሥጋና የእግዚአብሔር ሀብቱ ነውና እንኳን አስተዋይ አእምሮ ያለው ፍጥረት ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት ሳይቀሩ ያመሰግኑታል።
“የሦስቱ ልጆች መዝሙር” በሚለው ቅ/ገብርኤል ከእሳት ባዳናቸው ሕጻናት ጸሎት ላይ ዕጽዋት እና እንስሳት እንዲሁም ሌሎች ፍጥረታት በሙሉ እግዚአብሔር እንደሚመሰግኑ ተጽፏል። “እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ የተመሰገነ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ ያለ ነው” ካለ በኋላ ፍጥረታቱንይዘረዝራል። እነርሱም፦
 • ፀሐይ ጨረቃ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣  
 • በሰማይ ያሉ ኮከቦች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • የበጎ ጠል የበጎ ዝናም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • ነፋሶች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል
 • እሳት ዋዕይ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 •  መዓልትና ሌሊት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣  
 • የክፉ ጠል የክፉ ጤዛ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • ብርድ ውርጭ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • ብርሃን ጨለማ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣  
 • ደጋ ቆላ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • በረድ ጉም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • መብረቅ ደመና እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • ምድር እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች
 • ተራሮች ኮረብቶች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • በዚህ ዓለም የሚበቅሉ አትክልት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • ጥልቆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • ባሕር ፈሳሾች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • በውኃ ውስጥ የሚመላለስ ፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • በሰማይ የሚበሩ ወፎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • አራዊት እንስሳት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • የአዳም ልጆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • እስራኤል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • እግዚአብሔር የሾማቸው ካህናት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • የእግዚአብሔር ባሪያዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣
 • የጻድቃን ሰውነታቸውና ልናቸው እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣ 
 • የቀና ልቡና ያላቸው ጻድቃን … እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፣ እርሱ የተመሰገነ ነው ለዘላለምም ከፍ ከፍ ያለ ነው ይላል (የሦስቱ ልጆች መዝሙር ቁጥር 27-83)። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ፀሐፊው ብዙ ነገሮችን እያነጻጸረ አቅርቧል። መዓልትን ከሌሊት፣ ደጋን ከቆላ ወዘተ ወዘተ። እያንዳንዳቸው ቢዘረዘሩ ብዙ ነገር ይወጣቸዋል። የተጋ አንባቢ “ሥነ ፍጥረት” የሚለው የሊቁን የሞገስ ዕቊበ ጊዮርጊስን መጽሐፍ ያንብብ።
እግዚአብሔርን ስለ መግቦቱ እና ጠብቆቱ ሁሉ እንዲህ እያመሰገንነው በጎ ያደረጉልንን ባለውለታዎቻችንንም ማመስገን ብንለምድ እንዴት መልካም ነበር። ከልጅነት ጀምሮ እስከ ዕውቀት በየሕይወታችን እርከን አሻራቸውን ጥለው ያለፉ ብዙ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰዎች አሉ። በብዙው ሰው ዘንድ ወላጆችን ማመስገን፣ በተለይም እናትን ማመስገን፣ የተለመደ እና በየዘፈኑም በየእንጉርጉሮውም “እናቴ” እየተባለ የተነሣ ስለሆነ እዚህ መድገሙ መደረት ይሆናል። ከወላጆቻችን፣ እና ከቤት ቤተሰቦቻችን በተጨማሪ “እናመሰግናለን” ልንላቸው የሚገቡም ብዙ ናቸው። እንደ ባህል ሆኖ “እናመሰግናለን፣ አመሰግናለሁ” ማለትን አፋችን አልተለማመደውም። ውጪ አገር ከመጣን በኋላ በትንሹም በትልቁም “ቴንኪኪኪኪኪው” (ወንድ)፣ “ቴንኪውውውዉዉዉዉ” (ሴት) የሚሉንን እንደ “ፉገራ” የምንቆጥርበት አጋጣሚም እንዳለ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹን በአማርኛ አምተናቸዋል። ምክንያታችን “ለምዶባቸው እንጂ ከልባቸው አይደለም” የሚለው ነው። ቢሆንም አመሰግናለኹ ማለት ባይጠቅምም አይጎዳምና በጎ የሠሩልንን እናመስግን።
ወደ በዓሉ ስንመለስ፣ ይኼ በዓል በየዓመቱ መምጣቱ ካልቀረ፣ እኛም እዚህ መኖራችን ካልቀረ (ዕድሜ ይስጠንና)፣ እንዲህ ዝም ብለን ባናልፈው ጥሩ ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊ አድርገንም ቢሆን ማክበር ብንችል ጥሩ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ “የምስጋና” ቀን በመሆኑ በቤተሰብ በዓልነቱ ብንቀበለው እና ከቤተሰባችንና ከወዳጆቻችን ጋር ተደስተን ብናሳልፈው ግሩም ይሆናል። በተለይም በዚህ አገር ቤተሰብ የመሠረትን ሰዎች የልጆቻችንን ልብ እንገዛበት ይመስለኛል፣ እነርሱም በጓደኞቻቸው መካከል በኩራት የሚናገሩት የበዓል አከባበር ይሆንላቸዋል፣ በት/ቤትም “በዓሉን እንዴት አከበራችሁ?” ሲባሉ የሚመልሱት አይቸገሩም ብዬ አስባለሁ።
በጾሙ ወራትም ቢሆን ግሩም ግሩም “በየዓይነቱ” ምግቦቻችንን ከሽነን ኢትዮጵያዊ “ቬጂቴሪያን” (vegan thanksgiving) በዓል ብናደርገው ባህላቸው ላይ አንድ ቅመም ጨመርንላቸው ማለት አይደለም? እንደዚህ ዓመቱ ዓይነት ፍስክ ወቅት ሲሆን ምርጥ ዶሮ ወጥ፣ ወይም ቀይ ወጥ፣ ጥብሳ ጥብሱን፣ ድፎ ዳቦውን ወዘተ ወዘተውን አድርገን ልክ እንደ አገራችን ማንኛውም በዓል ብናከብረው “ኢትዮጵያዊ ታንክስጊቪንግ/ Ethiopian Thanksgiving” ተብሎ ይጠራልናል። አስቴር በቀለ (2010) የተባሉ ፀሐፊ “Ethiopian American Thanksgiving” ሽልማት ያስገኘ ጽሑፍ ነው ያሉትን ማንበብ ችዬ ነበር። እርሳቸው የምግቡን ዝርዝርም አቅርበዋል። ግሩም ነው። እንግዲህ እንዲህ እንዲህ እያልን ባህላችንንም ለሌሎቹ ማስተዋወቅ ብንችል መልካም ነው።

መልካም የምስጋና በዓል ይሁንላችሁ!
እግዚአብሔር ይመስገን
   
Originally posted on:
Date: 11/23/11 
Time: 9:37 PM
Pacific Standard Time

3 comments:

Dawit Adane said...

ዲያቆን ኃሳቡ መልካም ነው ። ነገር ግን ከጾም ጊዛችን ጋር
እንዴት ይሄዳል? ጾም የተመስጦ የአርምሞ ጊዜ አደለም? አናመስግን አደለም ፤ ነገር ገን ክሽን ያለ ምግብ ስናዘጋጅ ደክመን ከጾም ጸሎት እንዳያወጣን። ደሞ ዛሬ በምን አለበት ያስገባነው ነገር ነው እያደረ የነበረውን እያጠፋ ያለው። አንድ ሰው አለ የምስጋ ቀን ነው የምን ጾም ነው ምናመሰግነው ፈጣሪን አደለም ይላል።
ባይሆን ግን አድ ወዳጄ ያጫወተኝ ነገር ነበረ ። ሚሰራበት ቦታ ጾመኛ እንደሆነ ያውቃሉ እሱ እዛ መስራት ከመጀመሩ በፊት መስሪያ በቱ ሁሌ እሮብ እሮብዋዜማ ላይ ነበረ ሚያከብሩት ። ነገር ግን እሱ ከተቀጠረ በኃላ እሱንጥለው ላለማክበር እሱም ሃይማኖቱን እና ስርአቱን ስላስተዋወቀ ቀደም ብለው ከእሱ ጋር አክብረውታል።
እኛ ምስጋናን ምናከብርባቸው ቀናት ባያንሱንም ነገር ግን ይህም ይጨመር ከተባለ ጾማችንን ሳይጋፋ ቢሆን፤ ፈረንጆቹ ቀድመው ካከበሩት እኛም እንደዛ ብናረገው ባይ ነኝ።

birku belachew said...

Dn Ephrem,I have concern about the fasting day or time beginning.It is already known that according to EOTC "Hidar 15" (November 24) the fasting starts.But,you already posted that November 24 is not considered as fasting day.It is not clear for me.I need your explanation.
Thank you in advance!

Adebabay A said...

ሰላም Biruk/ ቡሩክ፤

ስለ አስተያየትህ አመሰግናለሁ። ጥሩ ተመልክተሃል። ጽሑፉ በመጀመሪያ በ2011 ከዚያ በ2014 የተጻፈ ስለሆነ ነው እንደዚያ ያለው ነገር የተከሰተው። በዚህ ዓመት ብቻ ሳይሆን በተከታታይ 3 ዓመታት የሚውለው ጾም ላይ ነው። በ4 ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ከጾም ውጪ ይውላል። መልክትህ አመሰግናለሁ።

Blog Archive