Friday, April 21, 2017

3 ነጥቦች ስለ ማርያም መግደላዊት፣ ጴጥሮስ እና ዮሐንስ

. «ጌታን ከመቃብር ወስደውታል» (ማርያም መግደላዊት)
መግደላዊት ማርያም የትንሣኤው ምስክር የሆነች ሴት ናት። ያውም ከሁሉ በፊት። ወንጌላዊው ዮሐንስ ከጻፈልን ወንጌል ላይ እንደምናነበው መግደላዊት ማርያም መቃብሩ ባዶ ሆኖ ባየች ጊዜ በቅድሚያ ያሰበችው «ሙስና-መቃብር» (ማለትም በመቃብር መበስበስን) አጥፍቶ ተነሣ የሚለውን ሳይሆን አይሁድ አስቀድመው የተናገሩትን ሐሰት ነበር።
አይሁድ ምን አሉ? «እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም፦ ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት» ይለናል ወንጌላዊው ማቴዎስ (ማቴዎስ 2764) መግደላዊት ማርያም በርግጥም ያሰበችው የጌታን ሥጋ ከመቃብሩ ሰዎች እንደወሰዱት ነው። በርግጥ እንደ አይሁድ ደቀመዛሙርቱ ናቸው የወሰዱት ብላ አላሰበችም። ለዚያም ነው ወደ ሐዋርያቱ እየሮጠች ሔዳ «ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ፦ ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም» ያለቻቸው።

ለእነርሱ ከነገረች በኋላም ቢሆን ስለ ትንሣኤው ገና አላመነችም ነበር። በብርሃን ለተገለጹላት መላእክትም ደግማ ያንኑ «ወስደውታል» የሚለውን ሐሳቧን መናገሯን ልብ እንበል። «ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው» እንዲል።
በሦስተኛ ደረጃ ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸላትና ለምን እንምታለቅስ ጠየቃት። አዳምና ሔዋን ዕጸበለስን አድምተው በተደበቁ ጊዜ እግዚአብሔር ዳናውን እያሰማ መጥቶ «አዳም ወዴት ነህ?» እንዳለው ሁሉአላዋቂ ሥጋችንን መዋሐዱን ለማጠየቅ «አልአዛርን ወዴት ቀበራችሁት ሲል እህቶቹን እንደጠየቃቸው ሁሉ፤ አሁንም መግደላዊት ማርያም ለምን እንደምታለቅስ ቢያውቅም «ለምን ታለቅሺያለሽ» ሲል ጠየቃት።  ወንጌላዊው «ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው» ይላል፡
ይህች ሴት ጌታ በምህረቱ የጎበኛት ሴት ናት። ቅ/ሉቃስ «ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም» ሲል ገልጿታል (ሉቃስ 8፣2)። ማልቀሷ ከልብ የመነጨ ሐዘን እንጂ የይስሙላ አልነበረም። መቃብሩ ባዶ ሆኖ ካየች በኋላም እንኳን መሔድ ያልፈለገችው እና ያገኘችውን በሙሉ «ጌታዬን ወስዳችሁት ከሆነ» ያለችው ከፍቅሯ ብዛት ነው። የተደረገለትን ውለታ የማይዘነጋ ትልቅ ሰው ነው። እንደ መግደላዊት።
ምንም እንኳን ውለታዋን ያልዘነጋች ሴት ብትሆንም በክርስቶስ ጠላቶች ወሬ መታለሏንም ልብ እንበል። «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው» እንዲሉ አበው። ሃይማኖታችንን በማይናወጽ አለት ላይ ካልመሠረትነው ሌሎች ሰዎች በሚዘሩት አሉታዊ አስተሳሰብ ልንጎዳ እንችላለን። እምነታችንን ከሰይፍ ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ከወሬ እና ከክፉ ትምህርት መጠበቅ ይገባናል። «አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና» እንዳለው ጠቢብ ሰሎሞን (ምሳሌ 423)።
 ፪ኛ. ወደ መቃብሩ ቀድሞ ደረሰ፣ ቀድሞ ግን አልገባም
መግደላዊት ማርያም ስለ መቃብሩ ባዶ መሆን ከነገረቻቸው በኋላ «ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር (ዮሐንስ) ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤  … ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ»። (ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለራሱ ሲናገር «ሌላው ደቀመዝሙር» ማለቱን ልብ በሉ።)
ዮሐንስ ወጣት ነው። ጴጥሮስ ግና ዕድሜ የጠገበ አረጋዊ ነው። ስለዚህም ወጣቱ ዮሐንስ አረጋዊውን ቀድሞ ወደ መቃብሩ በሩጫ ደርሷል። ነገር ግን ትሑት ነውና አረጋዊው ቀድሞ እንዲገባ ከመቃብሩ ደጅ ሆኖ ጠበቀው። ቄስ እያለ ዲያቆን መቅደም ስለሌለበት፣ ኤጲስ ቆጶስ እያለ ቄስ መቅደም ስለሌለበት ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ አረጋዊው መቅደሙ ተገቢ ነውና ወጣቱ ቅዱስ ዮሐንስ አረጋዊውን ጠበቀው። ትህትና። ስለ ዕድሜ ብቻም ሳይሆን ስለ ሥልጣነ ክህነትም የሚቀድመውና የሚከተለው ማን መሆን እንዳለበት ይህ ምዕራፍ ያስተምረናል።

፫ኛ. አየ፥ አመነ - ሐዋርያው ዮሐንስ
ሐዋርያት ጌታችንን ከዋለበት እየዋሉ፣ ካደረበት እያደሩ፣ የቃሉን ትምህርት - የእጁን ተአምራት ዩና የሰሙ ቢሆንም ልቡናቸው ገና በእምነት አልጸናም ነበር። ስለ ትንሣኤው የተማሩ ቢሆኑም «ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበር።» ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ግን «በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም» (ዮሐንስ ፳፣፰) ተብሏል። ፍቁረ እግዚእ፣ ጌታ ይወደው የነበረው፣ ያ ደቀመዝሙር ዘመኑን በመስቀል ላይ በአደራ የተሰጠችውን የጌታን እናት ወደ ቤቱ በመውሰድ፣ በዕለተ አርብ ያየውን መከራ በማሰብ በሐዘን የተቋጠረ ፊቱ ሳይፈታ በገድል በትሩፋት ኖሯል።
እኛስ ምን ዓይተን ነው የምናምነው ቢባል የሐዋርያትን ዐይን ዓይናችን አድርገን መከራ መስቀሉን የተቀበለውን ጌታ በዓይነ ኅሊናችን እንመለከተዋለን። በልባችንም የተደረገልንን ውለታ እና የተከፈለልንን ዋጋ እናስባለን። በቅዳሴያችንም «የማይደፈር ግሩም ነው፤ በእኛ ዘንድ ግን ጥሁት ነው። የማይገኝ ልዑል ነው፣ በኛ ዘንድ ግን አርአያ ገብርን (የባርያውን አርአያ) ነሣ። የማይዳሰስ እሳት ነው፣ እኛ ግን አየነው ዳሰስነውም፤ ከእርሱም ጋር በላን ጠጣን» እያልን እናመሰግነዋለን (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 88)። የሐዋርያትን ዓይን ዓይናችን አድርጎ ጌታን ማየት ማለት ይህ ነው። «ንሕነሰ ርኢናሁ ወገሠሥናሁ፣ በላዕነ ወሰተይነ ምስሌሁ»። (ዝኑ ከማሁ)
በአማን ተነሥዐ እሙታን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር  

3 comments:

Matiwos Tekalign said...

Kale Hiwot Yasemalin! Gn minew betam tefah? Bertalin Enji!

Matiwos Tekalign said...

Kale Hiwot Yasemalin memhir! gn minew Betam tefah?

eshete berju said...

egziabher zemenhn ybark