Tuesday, May 16, 2017

ሦስቱ የቤታችን «አርዕስተ ኃጣውዕ»፡- ሙስና፣ ዘረኝነት (መለካዊነት) እና የተሐድሶ ቅሰጣ

- አንዱ ከአንዱ ጋር ይመጋገባል፣
- አንዱ ለሌላው ማደግ እና መጎልበት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል፣
- ቤተ ክርስቲያናችን በነዚህ ሦስት ጦሮች ተሰቅዛለች፣
አጠቃሎ
በዚህ ዘመን ያሉት መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተናዎች ዓይን ያወጣ ዝርፊያና ጉቦ (ሙስና)፣ በወንዘኝነት ላይ የተመሠረተ ጥቁር ዘረኝነት እና እርሱ የወለደው መለካዊት እንዲሁም የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት ለመበረዝ እየተስፋፋ ያለ ኑፋቄ («ተሐድሶ») ናቸው። ይህ ማለት ሌሎች ችግሮች የሉብንም እነዚሁ ብቻ ናቸው ከሚል ደፋር ድምዳሜ የመጣ ሳይሆን አንኳር የሆኑትን እና እርስበርሳቸው የሚመጋገቡትን ችግሮች ለማንሣት ያደረግኹት ሙከራ መሆኑን በማሳሰብ ልጀምር።
በርዕሴ ላይ እንዳስቀመጥኹት መምህራን «አርዕስተ ኃጣውዕ» ብለው የሚያስተምሩት ሰይጣን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረባቸው እና መድኃኒታችን ድል የነሣቸውን ፈተናዎች መሆኑን አንባብያንን ላስታውስ። እነዚህ ሦስት የኃጢአት ራሶች («አርዕስተ ኃጣውዕ») የሚባሉት ትዕቢት፣ ፍቅረ ንዋይ እና ሥሥት ናቸው። ጌታችንም ትዕቢትን በትሕትና፣ ሥሥትን በትዕግስት፣ ፍቅረ ንዋይን በጸሊአ ንዋይ ድል በመንሣቱ ለእኛ አርአያ ሆኖናል። (ማቴ፬፡፲፩) ዛሬ ደግሞ ድል ልንነሣቸው የሚገቡን ሦስቱ ፈተናዎቻችን ሙስና፣ ዘረኝነት እና ኑፋቄ ተጋርጠውብናል።

 ሐቲት
ሙስና እና ክርስትና እጅግ ተቃራኒ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው። አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ ተባብሮ ሊሄድ አይችልም። የሃይማኖት አንዱ ዓለማ እንዲህ ካለው ነፍስንም ሥጋንም ከሚያበላሽ ኃጢአት አማኙን መጠበቅ ነው፡፡ የሃይማኖት መምህራን በተለይ ደግሞ አማንያን «ያለን ይበቃናል» የሚለውን ሐዋርያዊ ትምህርት ገንዘብ አድርገው በላባቸው ደክመው እንዲኖሩ፣ የሌላውን ሰው ሀብት እንዳይፈልጉ፣ ድንበራቸውን አውቀው እንዲኖሩ እና ጊዜያዊ በሆነው ዓለም ኑሮ ድካም ተጠምደው ዘላለማዊውን ሕይወት እንዳያጡ መምከርና ማስተማር ነው። በርግጥም ምእመናኑ ከሞላ ጎደል ይህንን ትምህርት ተቀብለው ለብዙ መቶ ዓመታት ኖረዋል። አሁንም በዚህ ቃል ለመኖር ይሞክራሉ።
ይሁን እንጂ የዚህ ትምህርት ምንጭ እና ባለቤት ሆነው የሥነ ምግባር መለኪያና መዳልው መሆን የሚገባቸው ሰዎች እና የዚህ ትምህርት አስፋፊ የሆነችው ተቋም ራሷ በሙስናው በመጠመድ ግንባር ቀደም ሆነው ሲገኙ ችግሩ ከተራ ችግርነት ወጥቶ «የኃጢአት ራስ» ከመባል ደረጃ ይደርሳል። የአንድ ግለሰብ ኃጢአት የባለቤቱ እና የፈጣሪው ፈንታ ነው። ችግሩም የግለሰቡ ብቻ ነው። ይሁንና አንድ ግለሰብ የራሱን ድካም የተቋም ድካም በሚያደርግበት ወቅት ችግሩ በግለሰቡ እና በአምላኩ መካከል ብቻ እንዲቀር የሚተው የግል ጉዳዩ ሳይሆን የብዙዎች ሰዎች ችግር ይሆናል። ስለዚህም «አመልህን በጉያህ፣ ስንቅህን በአህያህ» እንደተባለው በጉያው መያዝ ያለበትን አመል በአደባባይ ሲያወጣው ጉዳዩ የሁላችንም ይሆናል። ለዚህም ነው ትንሽም ይሁን ትልቅ የኃላፊነት ወንበር ላይ የሚቀመጡ ሰዎች በጎም ይሁን መጥፎ ተግባራቸው የእነርሱ ብቻ ጉዳይ አይደለም የሚባለው።
በየቀኑ የሚወጡ ዘገባዎች ያለማወላወል እንዳረጋገጡልን ሙስና የቤተ ክህነታችን ትልቁ ችግር ሆኗል። ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በቅርቡ እንደተናገሩት ችግሩ «ከአቅሜ በላይ ነው» ብለዋል። የፈቀድነውን ያህል መንገድ ሄደን ነገሩን ለማድበስበስ ብንሞክርም ችግሩ ፈጥጦ የወጣ ስለሆነ ልንደብቀው የምንችለው አይደለም። «ቂጣ ከሆነ ይጠፋል፣ ሽል ከሆነ ይገፋል» ብለን ነበር ቂጣ አለመሆኑ እርግጥ ሆኗል። ስለዚሁ ጉዳይ በዝርዝር የተጻፈ «የሐራ ተዋሕዶ» ሪፖርታዥ ጉቦ፣ እጅ መንሻ እና ዝርፊያ ያለምንም ሀፍረት የሚፈጸምባት ቤተ ክህነት ታቅፈን ተቀምጠናል። (ሊንኩን እነሆ)
ጉቦው በደረጃ በደረጃ የተቀመጠ ሲሆን ለየትኛው የሥራ መስክ ስንት ሺህ ብር እንደሚጠየቅ ሪፖርታዡ በዝርዝር አቅርቧል። እንዲህ ያለ የተደራጀ የዝርፊያና የሌብነት ወንጀል በቤተ ክህነቱ መዋቅር በይፋ እየተፈፀመ ነው። ሪፖርቱ አዲስ አበባ ላይ ተመርኩዞ የተሠራ ቢሆንም በሌሎቹም አህጉረ ስብከት ተመሳሳይ በሽታ መዛመቱ ይታወቃል።
ይህንን የሚያነብ ማንም በጎ ልቡና ያለው ሰው «እንዴ፣ መንግሥት የለም እንዱ? ሕግ የለም እንዴ» ብሎ መጠየቁ አይቀርም። ይኸው ጥያቄ ነው ሁለተኛው «የኃጢአት ራስ» ጎትቶ የሚያመጣው። ይህም «መንደርተኝነት፣ ዘረኝነት፣ መለካዊነት» የተባለው በሽታ ነው።
መንደርተኝነት እና ዘረኝነት በቤተ ክህነቱ ዛሬ የመጣ አዲስ ክስተት አይደለም። እንደዚያ ብንል ሐሰተኞች ያስብለናል። ችግሩ ሥር የሰደደ ነው። በሥልጣን ላይ ሲቀመጡ የራስ አውራጃ ሰዎችን ብቻ መሰግሰግ፣ የሌሎች አካባቢ ሰዎችን ሰላም መንሣት፣ ከቤተ ክህነት ኃላፊነት እስከ አጥቢያ አለቃነት በየተመደቡበት የራስን ወገን ብቻ መሰብሰብ የነበረ አሁን ግና አድጎና ሰልጥኖ የተስፋፋ በሽታ ነው።
የዚህን ዘመን ዘረኝነት የተለየ የሚያደርገው በሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም እና ዓላማ ጋር የሚስማማ መሆኑ ነው። በቋንቋ ማንነት ላይ የተመረኮዘው የኢሕአዴግ ሥርወ መንግሥት ሰዎችን የሚያውቃቸው በቋንቋቸው ማንነት ላይ ብቻ ተመርኩዞ በመሆኑ ቤተ ክህነቱ ውስጥ ድሮም ተደብቆ ለነበረው ችግር መፈንዳት እና ዋነኛ በሽታ መሆን ዕድል ፈጥሮለታል። ስለዚህ በዓለም ካለው ዘረኝነት የባሰ በመንፈሳዊው ዓለም ባሉ ሰዎች ላይ ሰልጥኖ መገኘቱ የአደባባይ እውነታ ነው። (ለአብነት በውጪው ዓለም ያለውን የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ማንነት፣ የትኛው ቤተ ክርስቲያን የየትኛው ክፍለ ሀገር ሰዎች እንደሆነ እናውቀው የለ?)። ይህ የሃይማኖቱ ተቋም አንቀሳቃሽ ሞተሮች ድቀት ለተቀረው አማኝ ምን ትምህርት ያስተምራል ብንል መልሱ ቀላል ነው። የሃይማኖት ሰዎች እንዲህ ከሆኑማ …. በሚል የራሱን ድካም መሸፈኛ ያገኛል።
ሙስናውና ዘረኝነቱ በበኩሉ ለሌላ ችግር ትልቅ ቀዳዳ ከፍታል። ለሃይማኖት ቀሳጢዎች፣ ምዕመናንን ከበረተቸው ለመንጠቅ ለሚፈንጉ ሰዎች እና ከውስጥም እምነታቸውን ለቀየሩ መናፍቃን ዕድል ይሰጣቸዋል። በዚህ ዘመን «ተሐድሶ» የተባለው እና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን በምዕራባውያን ፕሮቴስታንቶች አስተምህሮ ለመቀየር ለሚለፋ ትልቅ ዘመቻ ያጋለጠን ይኸው ችግራችን ነው።
«ተሐድሶ» የተባለውንና የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን አዕምሯቸውን በመቀየር እና በማስኮብለል ቤተ ክርስቲያኒቱን ለቅቀው ሳይወጡ ነገር ግን ትምህርቷን በመለወጥ የመውረስ ዘመቻን በተመለከተ ከዛሬ ፳ ዓመት በፊት ጀምሮ በደንብ አውቀዋለሁ። ያን ጊዜ በዚህ ቅሰጣ ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ሰዎች ዓላማ፣ ግባቸውን እና መዋቅራቸውንም ጭምር። በሁለት እግሩ ለመቆም እና ቤተ ክርስቲያናችንን ለመለወጥና ለማበላሸት የነበረው ጥረት ሲመክን እና እንደገና ሲያንሰራራም ተመልክቼዋለኹ። ለማንሰራራቱ ደግሞ ዋነኛ ደጋፊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ዘረኝነት እና ሙስና ግንባር ቀደም መሆናቸውን ተመልክቻለሁ። ሙስናውና ዘረኝነቱ በተንሰራፋበት ተሐድሶን ለብቻው መዋጋት የተነሣውን ሰደድ ጋብ ያደርገው ካልሆነ በስተቀር አያጠፋውም። ተሐድሶን የሚያፋፋው «ለም-አፈር እና ውኃ» ካልተቋረጠበት በስተቀር መብዛቱ ላይቆም ይችላል። ለዚህም ነው የእምነት ችግር ያለባቸው ብዙ ወገኖች ከሙሰኛው እና በዘረኝነት ከተበላሸው የቤተ ክህነት ቡድን እና የዘመኑ አመለካከት ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ የሚሠራው። የእምነት ችግር የሌለባቸው ነገር ግን በዘረኝነታቸው እና በሥነ ምግባር ጉድለታቸው የሚታወቁ ሰዎች ለእምነታቸው አጥፊ ለሆኑ ሰዎች ረዳት ሲሆኑ የምንመለከተው በዚሁ ሰበብ ነው።
ተሐድሶን ለመግታት ትልቅ ርብርብ እየተደረገ ነው። ተገቢ እና ጊዜ የማይሰጠው ነው። ሌሎቹን ችግሮች ሳይመለከቱ እዚህ ላይ ብቻ አቅምን በሙሉ ማጥፋቱ የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም። ለሌሎቹም ችግሮች ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለብን። በእኛ ዘንድ ያለው የሙስና ችግር በሌላው ዓለም ቢሆን ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ አገር-ቀጥ የሚልበት በሆነ ነበር። ካቶሊኮች ሕጻናት ልጆችን በማባለግ (ፔዶፊሊያ) በመላው ዓለም እንደገቡበት ያለ ትልቅ አዙሪት (ክራይሲስ) ላይ ነን። ይህ አባባል የሚያስከፋቸው ብዙ ሰዎች ቢኖሩም እውነታው ግን ይኸው ነው። በአገራችን ያለው የሕግ አስፈጻሚው አካል ቤተ ክርስቲያን ላይ የታወጀውን የዝርፊያ አዋጅ ሊከታተል እና ወንጀለኞችን ሊያስቆም ሲገባው የቤተ ክርስታኒቱ መዳከም ይጠቅመኛል በሚለው የቆየ ክፉ አመለካከቱ ምክንያት ችግሩ እንዲስፋፋ ትቶታል። (ብዙዎቹም ሙሰኞች የዚሁ ፓርቲ አባላትና አካላት መሆናቸው የታወቀ ነው።)
እነዚህ ሦስት ፈተናዎች ለዚህ ዘመን የቀረቡ ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው። የምንሰጠው መልስ የወደፊት አገራዊ እና ሃይማኖታዊ ማንነታችንን ይወስናሉ። በእሳት የተያያዘ ሰው ተቃጥሎ ሕይወቱን ባያጣም እንኳን ለቀሪ ዕድሜው ምልክት የሚሆነው ጠባሳ ሳይተርፈው አይቀርም። የጊዜያችን ሙስና፣ ዘረንነት እና ኑፋቄ በአማንያን ሕይወት ላይ ጠባሳውን ሳያሳርፍ ያልፋል ብለን መገመት የዋህነት ነው። እሳቱ ጨርሶ እንዳይበላን ግን ማድረግ ይቻላል።

ይቆየን
   
    


2 comments:

Matiwos Tekalign said...

Engdih Yetfat Erkuset Bemekdesu komo stayu Anbabiw Yastewl!
Kalehiwot Yasemalin!
EF minew betam Eyetefah new? Berta enji.

Anonymous said...

በአገራችን ያለው የሕግ አስፈጻሚው አካል ቤተ ክርስቲያን ላይ የታወጀውን የዝርፊያ አዋጅ ሊከታተል እና ወንጀለኞችን ሊያስቆም ሲገባው የቤተ ክርስታኒቱ መዳከም ይጠቅመኛል በሚለው የቆየ ክፉ አመለካከቱ ምክንያት ችግሩ እንዲስፋፋ ትቶታል። (ብዙዎቹም ሙሰኞች የዚሁ ፓርቲ አባላትና አካላት መሆናቸው የታወቀ ነው።)