Wednesday, July 12, 2017

ሳውል-ቅዱስ ጳውሎስ፤ ከደማስቆ በር እስከ ቀጥተኛይቱ መንገድ

ጠቅለል ያለ መግቢያ ስለ ሳውል ….
(ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ)
ቅዱስ ጳውሎስ የቀደመ ስሙ ሳውል ነው። አይሁዳዊ ነው። የተማረና ሊቅ፤ ለይሁዲነቱ እና ለእምነቱ ታላቅ ቅንዓት ያለው ሰው ነበር። በመምህሩ በገማልያል እግር ስር ተቀምጦ የተማረ ምጡቅ ሊቅ። ከቅንዓቱ የተነሣ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የሚተጋ ሰው። ትውልደ ነገዱ ከዕብራውያን ዘር ከብንያም ነገድ የተገኘ ሲሆን ሀገረ ሙላዱ (የተወለደበት) በንግዷ ታዋቂ በሆነችው በጠርሴስ ነው። ትውልዱ ዕብራዊ ቢሆንም አባቱ የሮማዊነትን ዜግነት የተቀበለ በመሆኑ ሳውልም ሮማዊ ዜግነት ነበረው ማለት ነው። ሮማዊ ዜግነት በዘመኑ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው የዜግነት መታወቂያ ነበር። በዘመናችን እንዳለው የየትኛው አገር ዜጋ (ፓስፖርት?) እንበለው ይሆን?
ይህ በትውልድ አይሁዳዊነት በዜግነት ደግሞ ሮማዊነት ያለው ሳውል የተባለ ሰው ገና በልጅነቱ ገማልያል በሚባል መምህር እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረ ሲሆን በመምህሩ አማካይነትም «ፈሪሳዊነትን» የተቀበለ ምሁር ሆኖ አደገ። በ30 ዓመቱ የአይሁድ ሸንጎ አባል መሆኑ የሚያሳየው ምን ያህል የተማረ እና ሕግ አዋቂ መሆኑን ነው። ጌታ ባስተማረበት ዘመን የነበረ ሰው እንደመሆኑ ስለ ጌታ ትምህርት፣ ስለ ሐዋርያቱ ስብከት ጠንቅቆ ያውቃል፤ ሰምቷልም።

ሳውል ባለው ዕውቀት ላይ ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ ሰው በመሆኑ ክርስቲያኖችን እና ትምህርታቸውን አጥብቆ ይጠላ ነበር። ስለዚህም በአፍ በመጣፍ ይከራከራቸዋል። ሕግ ሲፈቅድለትም በኃይል ይገዳደራቸዋል። ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ባረፈበት ወቅት ሳውል ከአስወጋሪዎቹ አንዱ መሆኑን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። እንዲህ ሲል፡- «ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም፦ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ፦ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።» (የሐዋ. 7፡58-60)
በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት ማኅበረ ክርስቲያኑ ተበትኖ ስደት ተጀመረ። ስምንት ሺህ የሚሆኑት ክርስቲያኖች ወደተለያዩ አገሮች ተበተኑ። ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም ያሳድዳቸው የነበረው ሳውል ክርስቲያኖች ከተበተኑም በኋላ ዕረፍት ሊሰጣቸው አልፈለገም። የሐዋርያት ሥራን የጻፈልን ቅዱስ ሉቃስ እንደነገረን «ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ» እንዲሰጠው ለመነ («የሐዋርያት ሥራ  9፡1)። ይህንን የማሳደድ፣ የማሰር፣ የመግደል ፈቃድ ካገኘ በርግጥም ፈቃዱ የሰጠውን መብት ለመተግበር ሙሉ መብት ያገኛል ማለት ነው። ይሁንና ይህንን ሐሳቡን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት እግዚአብሔር ቀደመው። ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ጽፎታል፡-
«ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ፦ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው። እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ፦ ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ? አለው። ጌታም፦ ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል አለው። ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቆሙ። ሳውልም ከምድር ተነሣ፥ ዓይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት። ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም አልጠጣምም።» (የሐዋ. 9፡1-9)

የሚያሳድደው ማን መሆኑ በደማስቆ ጎዳና፣ በደማስቆ መንገድ፣ በደማስቆ በር ላይ በተአምራት የተገለጸለት ሳውል ያ ሁሉ ዛቻውና ደብዳቤው መከነ። ሌሎችን እየመራ የሄደው ሰው ዓይኑ ማየት ተስኖት በሌሎች ይመራ ጀመር። ሌላውን ለመያዝ ጠንካራ የነበረ ክንድ አሁን የሚመራው ፈለገ።

ያለ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት «ሳውል» ተለውጦ «ጳውሎስ» አይሆንም ነበር …
«የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» የሚለው የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት መሬት ላይ ወድቆ አልቀረም። የወጋሪዎቹን ልብስ የጠበቀውና በመወገሩም የተስማማው ሳውል ጠፍቶ ያልቀረው በእስጢፋኖስ ጸሎት ነው። የቅዱሳን ጸሎት ሰዎችን ወደ እውነት እና ወደ ድኅነት እንደሚመራ ጥሩ ማስረጃ ነው። በጸሎታቸው እና በተገባላቸው ቃል ኪዳን ድንጋዩን ልብ ወደ ሰው ልብ ይቀይራሉ፤ ከአሳዳጅነት ሰውን ይመልሳሉ። ዓይነ ልቡናችን ተገልጦ እውነተኛውን አምላክ እና ሥራውን እንድናይ ያደርጋሉ፣ ጆራችን ብቻ ሳይሆን እዝነ ልቡናችን ተከፍቶ ድምፁን እንድንሰማ እና «ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» እንድንል ያበቁናል። ለክፋት፣ ለማሳደድ እና ሌሎችን አደጋ ላይ ለመጣል የሚያዩ ዓይኖች ተዘግተው የእግዚአብሔርን የቸርነት ጎዳና የሚመለከቱ ዓይኖች ይከፈታሉ። «ሳውልም በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ» እንዳልነበር አሁን ደግሞ በዚያም ሰማዕት ጸሎት የጌታው ቸርነት ተደርጎለታል።
የምዕራባውያን ክርስቲያኖች አባት የሚባለው አውገስቲን (አውግስጢኖስ) ነው «ያለ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ሳውል አይለወጥም ነበር» ያለው። እርሱ ራሱ አውግስጢኖስን ለመለወጥ ያበቃው የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት እና መለወጥ ታሪክ ጭምር ነው።  ቅዱስ ያዕቆብ እንዳለው «የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።» (የያዕቆብ መልእክት 516)

«ቀጥተኛ የሚባል መንገድ»
«ሰኮተ እንተ ይብልዋ ርትእት፣ ቅን/ቀጥተኛ የምትባለው መንገድ» …
ክርስቲያኖች ከገቡበት ገብቶ ከዋሉበት እንዳያድሩ፣ ካደሩበት እንዳይውሉ ለማድረግ ሊያሳድዳቸው ወደ ደማስቆ የተጓዘው ሳውል በተአምር - በመብረቅ ብልጭታ - የትዕቢት ልቡ ተሰብሮ፣ ዓይኑ በተአምራት ታውሮ ወደ ደማስቆ እንዲሄድ በጌታ በታዘዘ ጊዜ ሄዶ ያረፈበት ቦታ ልዩ ስሟ «ርትእት» ወይም በአማርኛ «ቀጥተኛ» የሚባል መንገድ ነው። እንግሊዝኛው «the street called Straight» ይለዋል።
«በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፥ ጌታም በራእይ፦ ሐናንያ ሆይ፥ አለው። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆኝ አለ። ጌታም፦ ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል።» እንዳለው ሁሉ ወደ ሳውል የተላከውን ሐናንያን ደግሞ «ተነሥተህ ቅን (ቀጥተኛ) ወደሚባለው መንገድ ሂድ፥ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ …»
አለው ይላል። (የሐዋ. 9፡10) ግእዙ እና እንግሊዝኛው ተስማምተው የሚገልጡት ቅን ከሚለው የአንዳንድ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ትርጉም ይልቅ «ቀጥተኛ» የሚለው «ርትእት» ወይም «Straight » ለሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም  ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ ከአሳዳጅነት ወደ ታዛዥነት ከተለወጠ በኋላ፣ ከአሳዳጅነቱ ጎዳና ወደ ታዛዥነቱ ጎዳና የተለወጠበት ውሳጣዊ ለውጥ፣ ባረፈበት ጎዳና/ street ስም ግሩም ሆኖ ይገለጣል። የጎዳናው ስም በግእዙ «ርትዕት» በአማርኛ «ቀጥተኛ» ተብሎ ተተርጉሟል። እንግዲያውስ «ቀጥተኛ» ወይም «ርትዕት» ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነታችን የምንሰጠው አንዱ መገለጫ ነው። እምነታችን ርትዕት እንደሆነችው ሁሉ ከሳውልነት ተመልሶ ጳውሎስ የተባለው ሐዋርያ ሕይወቱና ትምህርቱ ርቱዕ፤ እምነቱ ደግሞ ርትዕት ሆኗል። «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ፤ የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች የጸናች ናት፡፡» እንዲል። የእርሱ ብቻ ሳይሆን እርሱ ያስተማራቸው አባቶችም ሃይማኖታቸው «ርትዕት» ናት። የእርሱ ሃይማኖት ካለን የእኛም ሃይማኖት የሐዋርያት ሃይማኖት ናትና በርግጥም «ርትዕት» ሃይማኖት ነው የያዝነው።
ልክ በዚህ በእኛ ዘመን እንደሚደረገው እና ቤተ ክርስቲያናችን ክርስቶስን እና ክርስትናን የማታውቅ፣ እርሱ ያስተማረውን ወንጌል ተቀብላ የማታስተምር ኦሪታዊት እንደሆነች ስሟን ለማጠልሸት ሰፊ ቅስቀሳ ይደረግባት በነበረው በ16ኛው መ/ክ/ዘመን አጼ ገላውዴዎስ ስለ ሃይማኖቱ ምንነት በዘረዘረበት የሰኔ 23/1555 ዓ.ም «የሃይማኖት መግለጫው» ላይ እንዲህ አለ፡-
«…ወኢናጸንን ኢለየማን ወኢለጸጋም እም ትምህርተ አበዊነ፤ አሠርቱ ወክልኤቱ ሐዋርያት፤ ወጳውሎስ ፈልፈለ ጥበብ፤ ወሰብዓ ወክልኤቱ አርድዕት፤ ወሰለስቱ ምዕት አሰርቱ ወሰመንቱ ርቱዓነ ሃይማኖት ዘተጋብኡ በኒቅያ፤ ወምዕት ወሃምሳ በቁስጥንጥንያ፤ ወክልኤቱ ምዕት በኤፌሶን»
ማለትም
«እኛስ እውነተኛ በሆነው በጥርጊያውና በዋናው መንገድ እንሔዳለን፤ ከአባቶቻችን ትምህርት ወደ ግራም ወደ ቀኝም አናዘነብልም፤ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፤ የጥበብ ምንጭ ጳውሎስ፤ ሰባ ሁለቱ አርድዕት፣ በኒቅያ የተሰበሰቡ 318ቱ ኦርቶዶክሳውያን፤ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ 150ው፤ በኤፌሶን የተሰበሰቡ ሁለት መቶው …» (ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የጻፉት «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ» ገጽ. 176-181)

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዳሉት ይህ መግለጫ በንጉሱ ስም ይሁን እንጂ አዘጋጆቹ የእኛው ሊቃውንት ናቸው። መግለጫነቱም የእነርሱው ነው። እኛም የአባቶቻችን ልጆች ከሆንን የምናምነው ይኼንኑ ነው።

ማጠቃለያ
የቅዱስ ጳውሎስ ያለፈ ሕይወት መዘርዘር ያስፈለገው እግዚአብሔር ያከበረውንና ከሐዋርያት እንደ አንዱ የተቆጠረው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን ለመውቀስ አይደለም። እግዚአብሔር ያከበረውን መውቀስ አይቻልምና። ይልቁንም በጸሎቱና በአማላጅነቱ ተማጥነን ፀጋና በረከትን እንለምናለን እንጂ። ዓላማችን በእርሱ ሕይወት ነጸብራቅ እኛም መንገዳችንን እንድንፈትሽበት፣ የእግዚአብሔርንም ቸርነት እና ታጋሽነት እንድንመረምርበት ነው። «ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ፣ ኑሩ «ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ» ነኝ (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፥23) እንዳለው በሃይማኖት እና አባቶቻችን ባስተማሩት በወንጌል ተስፋ መጽናትን ገንዝብ እናድርግ።
የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ አማላጅነቱና ተራዳዒነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን፤

አሜን  

1 comment:

asbet dngl said...

አሜን ቃለ ሕይወት ያሰማልን!

Blog Archive