Monday, October 16, 2017

አገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት ማለት ምን ማለት ነው?

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ዘንድ ስልክ መታሁ። ኢትዮጵያ። ብዙ ጊዜ ስለ አገር ሁኔታ በስልክ ማውራት አልፈልግም። ወዳጄም እንደዚያው። በዚህ ስልክ ጥሪ ግን ወዳጄ በቀጥታ የገባው ወደዚሁ ጉዳይ ነው። «አገር ሊፈርስ ነው። በጣም ከባድ ጊዜ ነው። ሰዎቹ ነገሩ የገባቸው አይመስለኝም። ወይም አውቀው አገሪቱ ከጥፋት ላይ እንድትወድቅ እያደረጉ ነው» አለኝ። ብዙ ነገር ማለት አልፈለግኹም። «እግዚአብሔር ያውቅላታል እንግዲህ» አልኩት። «እሱ ብቻ ነው የቀረን ተስፋ» አለኝ። ድምፁ ያለውን ሥጋት በደንብ ያንፀባርቃል።
ከዚህ ስልክ ቀናት ወደም ብሎ ከሌላ ወዳጄ ጋር ተመሳሳይ ውይይት ነበረን። ይህኛው ወዳጄ «ኢትዮጵያ አድጋለች፣ በልጽጋለች» ባይ፣ ሌላ ምንም ዓይነት «ክፉ ነገር» ማውራት የማይፈልግ እንደሆነ አውቃለኹ። አገሪቱ ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር አለ ማለትን መሪውን ክፍል ከመቃወም ስለሚቆጥረው እንዲህ ያለ ነገር ካፉ አይወጣም ነበር። አሁን ግን ያንን ወገንተኝነቱን አልፎ «በጣም ከባድ ጊዜ ነው፤ ነገሮች ቋፍ ላይ ያሉ ይመስላል» ሲለኝ ደነቀኝ።  «የሆነ የሚፈነዳ፣ የታፈነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል» ነው ያለኝ ይህኛውም ወዳጄ።

የሁለቱን ወዳጆቼን አባባል ስገመግመው በየሚዲያው የምሰማውና የማነበውን «አገራችን መንታ መንገድ ላይ ናት» አባባል የበለጠ ማረጋገጫ ሆነልኝ። 2010 . ኢትዮጵያ እና የግንቦት 1983 . ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሆነዋል ማለት ነው። እንዲያውም በብዙ መልኩ 1983 .ምሕረቷ ኢትዮጵያ መሠረቷ የፀና ነበረች ማለት ይቻላል። 2010 ኢትዮጵያ ብዙ መሠረቶቿ የተነጋነጉባት እና የዘመኑ ዐውሎ ነፋስ ብዙ ጉዳት ሊያደርስባት የሚችልባት አገር እንደሆነች ይሰማኛል።
በዚህ ዘመን በአገራችን ሕዝቦች መካከል የተነዙ ብዙ መርዞች አሉ። አንድን ሰው በግለሰብነቱ ሳይሆን በሚናገረው ቋንቋ የመመዘን ደረጃ ላይ ተደርሷል። ሰዎች በዚሁ ማንነታቸው ከአንድ አካባቢ የሚባረሩበት፣ ገፋ ሲልም ሕይወታቸውን የሚያጡበት ዘመን ነው። ከአንድ ክፍለ ሀገር ወደሌላው መሔድ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር እንደመሔድ «የሚደነቅበት» ዘመን ነው። የመሐል አገር ሰው ወደ ሰሜን ስለሄደ ብቻ «ዜና» የሚሆንበት ዘመን ነው። አንዱ ብሔረሰብ ስለሌላው የሚያወራው ድሮ የአገራችን ሰው ስለ አውስትራሊያ ወይም ስለ አርጀንቲና እንደሚያወራው ዓይነት ሆኗል። በርግጥ 26 ዓመት ቀላል ለውጥ አላመጣም።
በዚህ አገራችን «መስቀለኛ መንገድ» ላይ መሆኗን እንኳን ምሁሩና አዋቂው ማንኛውም ተርታ ሰው በዓይኑ ማየት በሚችልበት ዘመን ነገሮች መስመር እንዳይስቱ ሊያደርጉ የሚችሉ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማት ግን የማዕበሉ መምጣት የታያቸው አይመስሉም። ወይም እንዳይታያቸው ተደርገው ስለተጠነፈጉ/ ስለተቀፈደዱ/ እግር ተወርች ስለታሰሩ ሕዝባቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ሊጫወቱት ለሚችሉት በጎ ሚና ዝግጅት እንዳያደርጉ ሆነዋል። 
የሚያሳዝነው በውጪው ዓለም ያሉት ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማትም በተመሳሳይ መንገድ ነገሩ የገባቸው አይመስሉም። ነገሩን ሁሉ ለፖለቲከኞች ትተዋል። ወይም የእነርሱ አጀንዳ አራጋቢ ብቻ ሆነው ቀርተዋል።
የቻይናዎች አባባል ነው በሚባለው ፍሬ ከናፍር እንደተገለፀው «ጨለማን ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት» ይሻላልና የዚህ ሁሉ አገራዊ ቀውስ ምክንያት የሆነውን 40 ዓመት ዘረኛ ፖለቲካችንን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ይኸው ፖለቲካ ይዞ ለሚመጣው ለማይቀረው ጉዳት መዘጋጀትም ያስፈልገናል። ትናነት «ኢትዮጵያ ሶማሌ» ክልል ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ከትናንት በስቲያ ከጋምቤላ እና «ኦሮሚያ» ክልሎች ዜጎች ሲፈናቀሉ እንዳየነው ሁሉ ነገ ደግሞ «ሁልህም ወደየክልልህ» ሲባል የሚፈጠረውን (ሰይጣን ጆሮው ይደፈንና) አገራችን ዓይታም ሰምታም የማታውቀው ቀውስ ሊኖረን ስለሚገባው ምላሽ መዘጋጀት የምንጀምረው መቼ ነውሌላው ሌላው ሁሉ ይቅርና የእምነት እና የማኅበረሰብ ተቋማት (ካሉ) የዕርቁ አካል መሆን እንዲችሉ ካሁኑ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ በውጪው ዓለም ያሉት የክርስትና እና የእስልምና ተቋማት የዚህ ዝግጅት መሪዎች መሆን ይችላሉ። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የእነርሱ ተከታይ ነው። ስለዚህ አማኛቸው የጥፋቱ አካል እንዳይሆን የሰከነ ውይይት ቢጀምሩ ደግ ነው። አገር ቤት ያሉት የእምነቱ መሪዎች ያንን እስኪያረጉ መጠበቁ አስተዋይነት አይመስለኝም።
በርግጥ አገር ቤት ያሉ የእምነት መሪዎች በዚህ ጊዜ ለአገራቸው ካልሆኑ ኋላ እሳት ለማጥፋት ጊዜ ቢመጡ ዋጋቸውን ይቀንሳሉ። እሳቱ እየመጣ እንደሆነ ካላወቁ በስተቀር። እነርሱን ለዚህ ነገር የሚያነሳሳ ማን እንደሚሆን እንጃለቱ። ራሱ ባለቤቱ ፈጣሪ ልቡናቸውን ይቀስቅስልን እንጂ።
በውጪውም ዓለም ያለን ሰዎች በአገራችን የዕለትተዕለት ጉዳይ ላይ ያለን ተጽዕኖ እጅግ አናሳ ቢሆንም በየቤታችን ሆነን ከምንቆዝም ግን የአቅማችንን ለማድረግ ማሰባችን አይከፋም። ቢቀር ቢቀር «ኢታርዕየኒ ሙስናሐ ለኢትዮጵያ .... የኢትዮጵያን ጥፋቷን አታሳየኝ» ብለን ጭንቀታችንን በጸሎት ወደ ፈጣሪያችን ማድረጋችንን መቀጠል አለብን። ይኸው ነው።

1 comment:

asbet dngl said...

መምህር ቃለ ሕይወት ያሰማልን ፣አባታዊ ምክርዎት ወቅታዊ አስፈላጊም ነው ።ግን ይህ ሊሆን ግድ ስለሆነ ሁሉም የፈዘዘበት ዘመን ነው ፣ አዱኛ ቄጣ ነች ወቅት ጠብቃ ትገለባበጥ አለች ። አሁንም ዋዜማው እየታየ ነው ።በፀሎት እንበርታ